የራያ እና የወልቃይት የማንነት እና እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን አስመልክቶ ከሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት 16 ቀን 2011 ዓ.ም

በትግራይ ክልል አላማጣ ከተማ የራያን ህዝብ የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ይዘው ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓም ሰልፍ በወጡ ዜጐች ላይ የክልሉ ልዩ ኃይል በወሰደው የሃይል እርምጃ ቢያንስ 9 ሰዎች በጥይት ተመተው መገደላቸውን፤ 16 ወጣቶች በጥይት መቁሰላቸውን፤ እንዲሁም ከ50 በላይ ወጣቶች እየተደበደቡ ታፍነው መወሰዳቸውን ምንጮች ለሰመጉ አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም ከ500 በላይ የሚሆኑ የአላማጣ ወረዳ ወጣቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በቆቦ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ከተገደሉት ሰዎች መካከል፡

  1. ነጋሲ እዮብ
  2. ካሳ ንጉስ
  3. መሀመድ ዋከዬ
  4. ሞላ አብርሃም እንደሚገኙበት የሰመጉ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ራያ ቀደም ሲል በወሎ ጠቅላይ ግዛት ውሰጥ የነበረ ሲሆን ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል ተጠቃሎ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል አስተዳደር ስር ይገኛል፡፡ ይህንን ተከትሎ ለበርካታ አመታት በቋንቋቸውና በባህላቸው የመታወቅ ብሎም የመጠቀም፣ የማዳበር እና የማስፋፋት ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው እንደተጣሰ በአዲስ አበባ የሚገኙ የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ ለሰመጉ አስረድቷል፡፡ የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ለሰመጉ እንደገለፁት ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ እየተፈፀሙ ያሉ የመብት ጥሰቶችን ለጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመንፈጉ ችግሩ ተባብሶ እዚህ ደረጃ ደርሷል፡፡

ራያ አላማጣ

 

የፌደራል መንግስት የራያ ህዝብ ያነሳውን ህገ- መንግስታዊ የማንነት ጥያቄ እና ከጥያቄው ጋር ተያይዞ እየተከሰቱ ያሉትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በሰከነ ሁኔታ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በተከተለ መንገድ እንዲፈታ ሰመጉ ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም መንግስት ከራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የዜጐችን በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነት እና የነፃነት መብቶች ላይ ጥሰት የፈፀሙ እና ያስፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ ሰመጉ ይጠይቃል፡፡

በሌላ በኩል የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ከዚህ ቀደም ”በኢ.ፌዲሪ ሕገ-መንግስት መሠረት የማንነት ጥያቄ በሚያነሱ ዜጐች ላይ የሚፈጸመው ግድያ፣ ሕገወጥ እስራት፣ አፍኖ መሠወር፣ ማፈናቀልና ንብረት መንጠቅ በአስቸኳይ ይቁም” በሚል ርዕስ 141ኛ ልዩ መግለጫውን ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓም ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ሰመጉ በመግለጫው የመጀመሪያ ክፍል የአማራ ብሔረተኝነት የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት 34 የወልቃይት ተወላጆች መገደላቸውን፣ 93 ሰዎች ታፍነው የደረሱበት አለመታወቁን ጨምሮ በተለያዩ ሰዎች ላይ ድብደባ ማሠቃየት፣ ሕገ ወጥ እስራቶች መፈፀሙን እና የእርሻ መሬት፣ መኖሪያ ቤትና ንብረታቸውን መነጠቃቸውንና ዜጎች መፈናቀላቸውን ዘርዝሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወልቃይትን ሕዝብ የማንነትና የታሪክ ጥያቄ ለማጥፋት የአካባቢውን ነባር የቦታ ሥያሜዎች በአዲስ ሥያሜዎች መቀየራቸውን የኮሚቴው አባላት መግለፃቸውን ጠቅሶ ሰመጉ በሪፖርቱ ይፋ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ከ141ኛ ልዩ መግለጫ በኋላም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በተለያዩ ጊዜያት በወልቃይት ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለሰመጉ ሲያመለክቱ ቆይተዋል፡፡

ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለተለያዩ ለሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትና ለኤምባሲዎች የተነጠቀ የአማራ ማንነታችን እንዲመለስልን ለ6ኛ ጊዜ የቀረበ አቤቱታ በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ ኮሚቴው ከ1974 ዓም ጀምሮ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ግፍና በደል ሲፈፀምበት ቢቆይም ለሕዝቡ ጩኸት መንግስት የሚጠበቅበትን ምላሽ እንዳልሰጠ አስረድቷል፡፡ የሕዝቡን ጥያቄ ለማፈን እያጋጠሙ ያሉ ወቅታዊ ችግሮች ናቸው በማለት ኮሚቴው በአቤቱታው ላይ ከዘረዘራቸው ችግሮች መካከል፤

 

ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላትን በፀረ ሽብር ሕግ በመክሰስና በማሰር ከቆየን በኋላ መንግስት ለሰላም ሲል በወሰደው እርምጃ ከእስር የተፈታን ቢሆንም አሁንም የኮሚቴው አባላት በየሄዱበት እየታሰሩ ነው፤ ሌሎች አባላትም ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸዉ በስደት ላይ ይገኛሉ፤

ከዚህም በተጨማሪ በወልቃይት ጠገዴ የሚኖሩ ዜጐች በአማርኛ ቋንቋ እንዳይነጋገሩና የአማርኛ ሙዚቃ እንዳይሰሙ እየተከለከሉ ነው፤ ይህንን ትዕዛዝ ጥሶ የተገኘ ሰው እየተደበደበና እየታሰረ ይገኛል፤

ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ የሚገኙ ወጣቶችና እና የማንነት ጥያቄ የሚያቀርቡ አዛውንቶች እየተደበደቡና እየታሰሩ እንዲሁም ከአካባቢያቸዉ እንዲሰደዱ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በተለይ በአሁኑ ሰዓት ጥያቄያችንን ለማዳፈን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ:: በዚህም ምክንያት ሕይወታችንና እንደ ህዝብ የመቀጠል ህልውናችን  አደጋ ውስጥ ገብቷል በማለት የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጠያቂ ኮሚቴ አባላት ለሰመጉ በአካል ቀርበው አመልክተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ አካባቢውን ጥሎ እንዲሰደድ የተለያዩ ጫናዎች እየተፈፀሙባቸው እንደሚገኝና የመከላከያ ሃይልና የፌዴራል ፖሊስ በቦታው ተሰማርቶ ከተጋረጠብን ከፍተኛ የአደጋ ስጋት ሊጠብቀን ይገባል ብለዋል፡፡

ሰመጉ የፌዴራል መንግስት ለወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር በአስቸኳይ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ፤ እንዲሁም የሰው ህይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉና ንብረት ያወደሙ አካላትን በአስቸኳይ ለህግ እንዲያቀርብ፤ ለተጐጂዎች ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፈልና የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ በማቋቋም ወደቀያቸው እንዲመልስ፤ ለደህንነታቸውም ዋስትና እንዲሰጥ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት አመታት የራያ እና የወልቃይት  ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የማንነት እና እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን በስፋት ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ለእነዚህ የማንነት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሁሉንም የፖለቲካ አካላት እና የዜጎችን ገንቢ ተሳትፎ ማረጋገጥ ለሀገር አንድነት ወሳኝ መሆኑን ሰመጉ ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም ለአመታት በአፈሙዝ ተዳፍነው የቆዩ ጥያቄዎችን በጥይት ሳይሆን በሕግ እና በስርዓት መፍታት ለዜጐች ሁለንተናዊ መብቶች መከበር ብቸኛው አማራጭ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ሰመጉ ያሳስባል፡፡

በመጨረሻም፤ መንግስት ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንዲሁም ለህግ የበላይነትና የፍትሕ ስርዓቱን ለማሻሻል የገባውን ቃል እንዲተገብርና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶችን እንዲያከብርና እንዲያስከብር ሰመጉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

መግለጫውን በፒዲኤፍ እዚህ ያገኛሉ

 

ሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ፀረ-ስቃይ ድርጅት (OMCT) አባል እና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

*

*