የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈፃሚዎች ላይ መንግስት በመውሰድ ላይ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!!

ሕዳር 04 ቀን 2011 ዓ.ም.

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሰኞ ሕዳር 03 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ አሰቃቂ ድርጊት የሚፈጸምባቸው 7 ድብቅ እስር ቤቶች መገኘታቸውን፤ ከእነዚህም በተጨማሪ በማረሚያ ቤቶችና በፖሊስ ጣቢያዎችም ጭምር በተጠረጣሪዎች ላይ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ እጅግ አሰቃቂ ድርጊቶች ሲፈፀሙ መቆየታቸውን ገልፀዋል። ከእነዚህ በህግ ጥላ ስር በሚገኙ ዜጐች ላይ ከሚፈፀሙት የማሰቃየት ድርጊቶች መካከልም የታሳሪዎችን ሰውነት በኤሌክትሪክ ሾክ ከማድረግ ጀምሮ ብልት ላይ ውሃ የያዘ የፕላስቲክ ኮዳ ማንጠልጠል፣ብልትን በፒንሳ መሳብ፣ ጥፍር መንቀል፣ ከአውሬ ጋር ማሳደር፣ ሴቶች ታሳሪዎችን መድፈር፣ በወንዶች ላይ ግብረሰዶም መፈፀም፣ እንዲሁም ደብዛን ማጥፋት በጉልህ የሚጠቀሱ በሕግ ጥላ ስር በተገኙ ዜጐች ላይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መሆናቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አረጋግጠዋል።

ኢሰመጉ (ሰመጉ) ባለፉት 27 አመታት ይህ ድርጊት በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፤ ሃሳብን የመግለፅ ሕገመንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሃሳባቸውን በነፃነት ሲያንሸራሽሩ በነበሩ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች፣ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰቡ አባላት ላይ እየተፈፀመ መሆኑን በማጋለጥ መንግስት የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ሲወተውት መቆየቱ ይታወሳል፡፡ መንግስት ለአመታት ለችግሩ ምላሽ መንፈግ ብቻ ሳይሆን የማሰቃየት ድርጊቶቹን ውጤት በመጠቀም የዜጐችን ሕገመንግስታዊ እና ሠላማዊ ጥያቄዎች በሃይል ሲያዳፍን ብሎም ንፁሐንን ሲያሸብር ቆይቷል፡፡ ይህንንም የማሸበር ድርጊት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ፊት በመቅረብ በግልፅ መናገራቸው እና ይቅርታ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ የማሰቃየት ድርጊቶች ለዜጐች ከለላ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው ፍርድ ቤት የተደበቀ እንዳልሆነ በፍርድ ቤቶች ውስጥ የማሰቃየት ድርጊት ሰለባዎች ለችሎት ከሚያቀርቡት የቃል እና የፅሁፍ አቤቱታዎች በተጨማሪ፤ ልብሶቻቸውን በድፍረት በማውለቅ አካላዊ ጉዳታቸውን ቢያሳዩም በፍርድ ቤቶች በኩል የተወሰዱ እርምጃዎች አለመኖራቸው ታይቷል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቶች የዜጐችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማስከበር ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ዜጐች እምነት አጥተውበት ቆይተዋል፡፡

ባለፉት 7 ወራት የመጣውን የመንግስት አስተዳደር ለውጥ ተከትሎ በመንግስት በኩል ሲወሰዱ የነበሩት እርምጃዎች በመልካምነታቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለይም ላለፉት 27 አመታት መንግስታዊ ሃላፊነትን ተገን በማድርግ በንፁሃን ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ በቆዩ የብሔራዊ ደህንነት የስራ ኃላፊዎች እና ድርጊቱን በቀጥታ ሲፈፅሙ በነበሩ ግለሰቦች ላይ እየተወሰደ ያለው ህጋዊ እርምጃ የሚደገፍ ነው፡፡ እስካሁን ከተወሰደው የማጣራት ስራ በተጨማሪም ተመሳሳይ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ እና ሲያስፈፅሙ የነበሩ ሌሎች የመንግስት ኃላፊዎችም ላይ እርምጃው እንዲቀጥል ሰመጉ ይጠይቃል፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፃሚዎች ላይ መውሰድ የጀመረውን ሕጋዊ እርምጃ በመደገፍ ረገድ፤ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ሰለባዎች ያሰባሰባቸውን መረጃዎች ለሚመለከተው የህግ አስከባሪ አካል መስጠትን ጨምሮ በማናቸውም መንገድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በተጨማሪም የማሰቃየት ድርጊቶቹ ሰለባ የሆኑ ዜጐች የደረሰባቸው አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ ጉዳት በቀላሉ የሚሽር እንዳልሆነ እሙን ነው። በመሆኑም ለተጐጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው ነፃ የህክምና፣ የስነልቦና ምክር አግልግሎት እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሰመጉ ይጠይቃል፡፡

በአጠቃላይ መንግስት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በፍጥነት ለፍትህ ማቅረቡ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው፡፡ይህ የፍርድ ሒደት መንግስት ከበቀል በፀዳ መልኩ ሕግን ብቻ መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ በማድርግ ላይ መሆኑን የሚያሳይበት፤ ዜጐች በፍርድ ቤቶች ላይ የተሸረሸረ እምነታቸውን የሚያድሱበት እና የሕግ ልዕልና የሚከበርበት የፍርድ ሒደት እንዲሆን ሰመጉ ይጠይቃል፡፡

መግለጫውን በፒዲኤፍ እዚህ ያገኛሉ

ሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ፀረ-ስቃይ ድርጅት (OMCT) አባል እና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

*

*