ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም
የዚህ ልዩ መግለጫ አቢይ አላማ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጉጂ ዞን በሚገኙ የተለያዩ
አካባቢዎች፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጌዴኦ ዞን በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም
በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ በሲዳማና ወላይታ ብሔረሰብ ተወላጆችና አባላት መካከል በተፈጠሩ ጥቃትና ግጭቶች ምክንያት
እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በበቂ ማስረጃ አስደግፎ በማቅረብ መፍትሄ እንዲሰጣቸው፣
ጥሰቶች እንዲቆሙና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ
ለማሳሰብ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ካሳ እንዲሰጣቸውና ድርጊቱን የፈጸሙና ያስፈጸሙ አካላት በህግ
እንዲጠየቁ፣ ጥሰት ፈጽሞ ሳይጠየቁ መቅረት እንዲቆምና ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች በድጋሚ
የማይፈጸሙበት የፖሊሲና የአሰራር ማስተካከያዎችና እርማቶች ከወዲሁ እንዲደረጉ መጠየቅና መጎትጎት
ነው፡፡
በተጨማሪም ይህ መግለጫ በማናቸውም መልኩ ለማንኛውም አይነት ጥቃትና ግጭት መቀስቀሻነት፣ ጥላቻን
ለመፍጠር እና ሠላምን ለማደፍረስ መዋል እንደሌለበት ሰመጉ ለሚመለከታቸው ሁሉ ያሳስባል። በመሆኑም
ይህ ልዩ መግለጫ ከላይ ከተዘረዘሩት አላማዎች ውጪ ህጋዊ ላልሆኑ እንዲሁም በጐ ህሊናን እና መልካም
ባህልን ለሚቃረኑ ተግባራት በሌሎች ወገኖች አማካኝነት ተግባር ላይ ቢውል የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ
ኃላፊነቱን አይወስድም።