በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ብሔር-ተኮር ግጭቶችን እና በቡድን የተደረጁ ኃይሎች እየፈፀሟቸው ያሉትን ከባድ ጥቃቶች መንግስት በአስቸኳይ ሊያስቆም ይገባል።

መስከ ረም 8 ቀን 2011 ዓ .ም

የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ሀገሪቱ በሁለት ተጻራሪ ሁነቶች ውስጥ እያለፈች
ትገኛለች። በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዷቸው መልካም ርምጃዎች ሀገሪቱ ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ ስጋት
ለጊዜውም ቢሆን ያስታገሰ፣ የዜጐች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ያበረታታ፣ እንዲሁም የዲሞክራሲን ጭላንጭል
የፈነጠቀ ነው። በአንፃሩ በራሳቸው በጠ/ሚኒንስትር አብይ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ጨምሮ፣ በተለያዩ አካባቢዎች
ህገወጥ ግድያዎች፣ ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ግጭቶች፣ የመንጋ “ፍትሕ” እና ስርዓት አልበኝነት በተለያዩ የሐገሪቱ
ክፍሎች እየተንሰራፉና ከዕለት ወደ ዕለት ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑ ነው። በአደባባይ ከተፈፀሙ ወንጀሎች እና የሰብዓዊ
መብቶች ጥሰቶች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፤

 • በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በ09/12/10 ጀምሮ ብሄርን መሰረት ያደረገ ግጭት ተከስቶ 3 ሰዎች ተገድለዋል፣
  በርካታ ንብረት ተዘርፏል፣ ቤት ንብረትም ተቃጥሏል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ በመግባት ግጭቱን ያረጋጋ ቢሆንም ዳግም ከ15/12/10 ጀምሮ ግጭቱ እንደ አዲስ በመቀስቀሱ ሌሎች 2 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
 • በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባሌ ዞን በጎባ ከተማና አካባቢው ከሀምሌ 13-16 2010 ዓ.ም. የተደራጁ ወጣቶች በፈፀሙት ጥቃት የ10 ሰላማዊ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፣
 • ደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የአካባቢው ህዝብ በሐምሌ 12 /2010 ዓ.ም. ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱለት ጠይቋል፡፡ ከዚሁ ሠልፍ ጋር በተያያዘ በተነሳ ረብሻ ወጣቶች የመንግስትና የህዝብ ንብረት ላይ ውድመት አድርሰዋል፡፡ በክልሉ በየም ልዩ ወረዳ ሀምሌ 15/2010 ለተመሳሳይ ጥያቄ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸውን ተከትሎ በተከሰተ ግጭት 6 ሰዎች ተገድለዋል፣ በርካታ ንብረትም ወድሟል፣ ደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ ከነሀሴ 5-6 2010 ዓ.ም. በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ የመልካም አስተዳደርና የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠይቋል በዚሁም እለት በተነሳ ግጭት 5 ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም ንብረት ወድሟል፣
 • በሻሸመኔ ከተማ በ6/12/2010 ዓ.ም. የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ አመራሮችን ለመቀበል በርካታ ህዝብ ወጥቶ ባለበት “ፈንጅ የጫነ መኪና መጣ” ተብሎ በተፈጠረ ግርግር 3 ሰዎች ተረጋግጠው ህይወታቸው ሲያልፍ፣ አንድ ሰው “ቦንብይዘሀል” ተብሎ በአሰቃቂና ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ተቀጥቅጦ ተገድሏል፣ አስከሬኑም አደባባይ ላይ ተዘቅዝቆ
  ተሰቅሏል፤
 • ከሀምሌ 28-29 2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል በተለያዩ ከተሞች በተለይም ጅግጅጋ፣ ዋርዴር፣ ጎዴ፣ ደጋሀቡር፣ ፊቅ፣
  ቀላፎ እንዲሁም ድሬዳዋ ውስጥ ብሄርን መሰረት አድርጎ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት በተፈፀመ የተደራጀ ሰፊ ጥቃት
  ከ100 በላይ የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ በበርካታ ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ 9 አብያተ ክርስቲያናት
  ተቃጥለዋል፣ በርካታ መኖሪያ ቤቶችና ንግድ ቤቶች ላይ ዝርፍያና ቃጠሎ ተፈጽሟል፤ከዚህ ጋር በተያያዘም በድሬዳዋ
  14 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤
 • በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በመዩ ሙለቱ ወረዳ ነሀሴ 13 2010 ዓ.ም ሮጌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተብሎ
  በሚጠራ አካባቢ የሶማሌ ልዩ ሀይል 31 የሚሆኑ ሰዎችን በጥይት ገድለዋል፤
 • ነሀሴ 18 2010 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ በፌዴራል ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ከይቅርታ አዋጅ አተገባበር ጋር
  በተያያዘ ባስነሱት አመፅ የ1 ታሳሪ ህይወት ሲያልፍ 3 የፖሊስ አባላት እና 3 ታራሚዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት
  ደርሷል፤
 • የአማራ የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል ተብለው 85 ሰዎች ኮረም ላይ የታሰሩ ሲሆን ሐምሌ 11 እና 18 ቀን 2010
  ዓም ዋጃ ላይ 3 ሰዎች፣ እንዲሁም ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓም ኮረም ላይ 1 ወጣት ተገድሏል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአላማጣ ወረዳ ከዋጃ፣ ጥሙጋ፣ ሰሌን ውሃ፣ ቢትሙ፣ ሀርሌ፣ አየር ማረፊያ እና በአጐራባች ቀበሌዎች ነሐሴ 285 ሰዎች ተፈናቅለው ራያ ቆቦ ወረዳ አልማ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።
 • በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን በመሰንቃና በማረቆ ማህበረሰብ መካከል የቀበሌ ይገባኛል ጥያቄ ቀርቦ ለረዥም ጊዜ መልስ
  ሳይሰጠው በመቆየቱ መስከረም 03 ቀን 2011 ዓም ከቆሼ ከተማ የጀመረው ግጭት እንሴኖና ቡታጅራ ድረስ ተስፋፍቶ እንሴኖ ላይ 3 ሰዎች ቡታጅራ ላይ 8 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በርካታ የመንግስት ተቋማት እና የግለሰቦች ንብረቶች ላይ ውድመት ደርሷል፡፡

ለዘመናት በበርካታ ችግሮች ተወጥራ የነበረችው ኢትዮጵያ በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘውን የዲሞክራሲ ጭላንጭል ሊጨልም ስር የሰደዱ ችግሮች እየተገዳደሩት ይገኛል። የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በበርካታ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ ችግሮችን በፍጥነት ለመቆጣጠርም ሆነ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በማጥናት ችግሮቹ ከመፈጠራቸው በፊት የመከላከል እርምጃ ሊወስድ አልቻለም። ለአመታት በውጭ ሃገራት የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን ተከትሎ የአቀባበል ስነ ስርዓቶቹን በተገቢው መንገድ ለመቆጣጠር በመንግስት በኩል የተደረገው ቅድመ_ዝግጅት ፍፁም ደካማ ሆኖ ታይቷል። በተለይም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን ለመቀበል ደጋፊዎቻቸው ያደረጉት እንቅስቃሴ እና ይህን ተከትሎ በመዲናችን በተለያዩ አካባቢዎች ከባንዲራ ጋር በተያያዘ የተነሱ ግጭቶች ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው አደጋ በግልፅ የሚታይ የነበረ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና የፌዴራል መንግስት በቂ ትኩረት ሊሰጡት አልቻሉም። መስከረም 05 ቀን 2011 ዓም የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል የተዘጋጀው ፕሮግራም በሰላም መጠናቀቁ የሚደነቅ ቢሆንም ምሽቱን በቡራዩ እና አካባቢው የሚኖሩ ንፁሃን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት የፌዴራልም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግስታት ለመቆጣጠር ባለመቻላቸው ዜጐች በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር-ተኮር ጥቃቱ ሠለባ እንዲሆኑ አስገድዷል።

ውጤቶች ናቸው፡፡ ለረዥም ግዜ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያው የሚሰራጩ ፀብ ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግሮች ዜጐችን ወደ
አልተፈለገ መስመር እየገፋ መሆኑ በግልፅ ቢታይም መንግስት ተገቢውን እርምጃ በወቅቱ ሊወስድ አልቻለም። በዚህም ባለፉት ቀናት ቡራዩ፣ በአሸዋ ሜዳ፣ ከታ እና አካባቢው የተፈፀመ ዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መንግስት በገለፀው መሠረት 25 ዜጐች ክቡር ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በተጨማሪም ቁጥራቸው በውል ላልታወቀ ሴቶችና ህጻናት መደፈር፣ ለበርካቶች አካል ጉዳት እና ከስምንት ሺህ በላይ ንፁሃን ከቤት ንብረት መፈናቀል አስከትሏል። ይፋ በመውጣት ላይ የሚገኙትና ጥቃቱን የሚያሳዩት ምስሎች የድርጊቱን አፈፃፀም ጭካኔ ብቻ ሳይሆን በቡድን የተደራጁ ኃይሎች እየተጓዙበት ያለውን አቅጣጫ ፍፁም አደገኝነት የሚያመለክቱ ናቸው።

ይህንን ተከትሎ በንፁሃን ዜጐች ላይ በተፈጸመው ጥቃት እና በፌዴራል መንግስት ዳተኝነት የተቆጡ የአዲስ አበባ ዜጐችም
ብሶታቸውን ለማሰማት በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ እና በአደባባዮች መስከረም 07 ቀን 2011 ዓም ተገኝተዋል። ይሁን እንጂ ሕዝባዊው ተቃውሞው ሠላማዊ የነበረ ቢሆንም የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የሃይል እርምጃ እስካሁን ድረስ ቢያንስ የአምስት ሠልፈኞች ህይወት ማለፉን ሰመጉ አረጋግጧል። በተያያዘም በዚሁ ዕለት በአርባ ምንጭ ከተማ በተደረገ ተመሳሳይ ህዝባዊ ተቃውሞ ስምንት ስዎች በጥይት የተመቱ ሲሆን የአንደኛው ግለሰብ ሕይወት ማለፉን ለሰመጉ የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡ (ሰመጉ ከመስከረም 05 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ በቡራዩ እና አካባቢው እንዲሁም መስከረም 07 ቀን 2011 ዓም በአዲስ አበባ እና በአርባ ምንጭ ከሠላማዊ ሠልፍ ላይ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የሀይል እርምጃ የደረሰውን የህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አጣርቶ ይፋ እንደሚያደርግ ከወዲሁ ይገልፃል)

የዜጐችን በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነት መብት፣ በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የመስራትና ንብረት
የማፍራት መብትን የማክበር እና የመጠበቅ ቀዳሚ ግዴታ የተጣለበት መንግስት ይህንን የዜጐች ሰብዓዊ መብት በማስከበር፣ ህገወጥነትን እና ስርዓት አልበኝነተን በመቆጣጠር በኩል ከፍተኛ የሆነ ቸልተኝነት አሳይቷል። ይህ ህዝባዊ ቁጣ ፈጣን ምላሽ ካላገኘ ፍፁም ወደ ሆነ ስርዓት አልበኝነት ላለመሸጋገሩ ምንም አይነት ዋስትና የለም።

በአጠቃላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ስያሜዎች ዛሬ ላለንበት ጅምር የዴሞክራሲ ስርዓት ክቡር ሕይወታቸውን
ሰውተው ያደረሱን ወጣቶች ለዘላቂ ሠላም ጠቃሚ ከመሆኑ አንፃር ወደ ህጋዊ አደረጃጀት እንዲገቡ ተደርጐ የተጠያቂነት
አሠራር እንዲኖር መንግስት ተገቢዉን እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል መንግስት የዜጐችን በህይወት
የመኖር፣ የአካል ደህንነት እና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በሙሉ ነጻነት የመንቀሳቀስ መብት በአፋጣኝ እንዲያስከብር፣
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች እና አስፈጻሚዎች ለሕግ እንዲያቅርብ፣ የሕግ የበላይነትን እንዲያሰፍን እና በአስቸኳይ
ሁሉን አቀፍ መፍትሔ እንዲፈልግ ሠመጉ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

መግለጫውን በፒዲኤፍ እዚህ ያገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

*

*