በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ እና በድሬደዋ ከተማ ከቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ በተፈፀመ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ – ነሐሴ 01 ቀን 2010 ዓም

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ውስጥ ከቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ በተፈፀመ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃትና ስርዓት አልበኝነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተፈፅሟል። በተፈፀመው ጥቃት በርካታ ዜጐች ተገድለዋል፣ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ተዘርፈዋል፣ በርካታ ንብረትም ወድሟል፤ በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አብያተ-ክርስትያናት በእሳት ተቃጥለዋል፡፡ በተደራጁ ወጣቶች የሚፈፀመውን ይህንን ጥቃት በመሸሽ በርካታ ዜጎች ለቀናት በቤታቸውና በቤተክርስትያን ውስጥ ተጠልለው ያለምግብና ውሀ እንዲቆዩ ተገደዋል። የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ጅግጅጋ ከተማ ከገቡ በኋላ አንፃራዊ መረጋጋት ታይቷል፡፡
ይሁን እንጂ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች አሁንም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። ለምሳሌም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጉና ገዶ ወረዳ ዱራሌ ተራራ አካባቢ የክልሉ ውሀ ቢሮ የሚያሰራው የውሀ መስመር ዝርጋታ ሠራተኞች የሆኑ 72 ዜጐች በአንዳንድ የአካባቢው ተወላጆች ዛቻ እየተፈፀመባቸው መሆኑን እና ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ለሰመጉ በስልክ አሳውቀዋል፡፡
ከዚሁ ጥቃት ጋር በተያያዘ በድሬዳዋ ከተማ አንዲት እናት እና አራት ልጆቿን ጨምሮ 14 ሰዎች መገደላቸውን ከአካባቢው ለሰመጉ የደረሰው መረጃ ያመለክታል። አሁንም ይህ ሪፖርት በሚጠናቀርበት ጊዜ ከፍተኛ ውጥረት በድሬዳዋ ከተማ ታይዋንና አሸዋ ሰፈር በሚባሉ አካባቢዎች ነግሷል የንግድ ሱቆችም ተዘግተዋል።

ይህን አሳዛኝና ኢሰብዓዊ ድርጊት ሰመጉ በጥብቅ እያወገዘ በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ዜጐች ቤተሰቦች ፣ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ እና ቤት ንብረታቸውን ለወደመባቸው ዜጐች መፅናናትን ይመኛል፡፡ ሰመጉ በጥቃቱ የደረሰውን የጉዳት መጠን መርምሮ ይፋ እንደሚያደርግ እየገለፀ፤ የዜጐቹን ደህንነት የመጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት በመስጠት የድርጊቱን ፈፃሚዎችና አስፈፃሚዎች በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፤ የህዝቡን ፍላጐት መሠረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግ ጥሪውን ያቀርባል። መላው ህብረተሰብም ከመንግስት ጋር በመተባበር የመፍትሔው አካል እንዲሆን ሰመጉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

በመጨረሻም የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ህግን ለማስከበርና ስርዓትን ለማስፈን የሚወስዱት እርምጃ በከፍተኛ ጥንቃቄና የሀላፊነት ስሜት እንዲሁም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባከበረ መልኩ እንዲሆን ሰመጉ ያሳስባል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ ፒዲኤፍ

ሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ፀረ-ስቃይ ድርጅት (OMCT) አባል እና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

*

*