Latest Posts

145ኛ ልዩ መግለጫ – በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ እና አካባቢው የተፈፀመ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት – ነሐሴ 03 ቀን 2010 ዓ.ም

የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በ145ኛ ልዩ መግለጫ የተመለከተው በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ሲሆን የመብት ጥሰቱ የተፈጸመው ከሕዳር 24 ቀን 2010 .ም ጀምሮ እስከ የካቲት 04 ቀን 2010 .ም ድረስ ነው።  ሰመጉ ባለሙያዎቹን ወደ አካባቢው ልኮ የማጣራት ሥራውን የሰራው ከየካቲት 05 እስከ የካቲት 12 ቀን 2010 .. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ወልደያ ከተማ፣ ወልደያ ዙሪያ ወረዳ፣ ቆቦ፣ ሮቢት፣ መርሳ፣ ውርጌሳ እንዲሆም በደቡብ ወሎ ደሴ የተፈጠሩት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርምሮ በዚህ መግለጫ አካቷል። በዚህም መሰረት የሰው ህይት እንደጠፋ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰ ሪፖርቱ በምስል አስደግፎ አቅርቧል። ሙሉ መግለጫውን በፒዲኤፍ እዚህ ያገኛሉ ።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ እና በድሬደዋ ከተማ ከቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ በተፈፀመ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ – ነሐሴ 01 ቀን 2010 ዓም

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ውስጥ ከቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ በተፈፀመ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃትና ስርዓት አልበኝነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተፈፅሟል። በተፈፀመው ጥቃት በርካታ ዜጐች ተገድለዋል፣ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ተዘርፈዋል፣ በርካታ ንብረትም ወድሟል፤ በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አብያተ-ክርስትያናት በእሳት ተቃጥለዋል፡፡ በተደራጁ ወጣቶች የሚፈፀመውን ይህንን ጥቃት በመሸሽ በርካታ ዜጎች ለቀናት በቤታቸውና በቤተክርስትያን ውስጥ ተጠልለው ያለምግብና ውሀ እንዲቆዩ ተገደዋል። የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ጅግጅጋ ከተማ ከገቡ በኋላ አንፃራዊ መረጋጋት ታይቷል፡፡
ይሁን እንጂ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች አሁንም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። ለምሳሌም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጉና ገዶ ወረዳ ዱራሌ ተራራ አካባቢ የክልሉ ውሀ ቢሮ የሚያሰራው የውሀ መስመር ዝርጋታ ሠራተኞች የሆኑ 72 ዜጐች በአንዳንድ የአካባቢው ተወላጆች ዛቻ እየተፈፀመባቸው መሆኑን እና ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ለሰመጉ በስልክ አሳውቀዋል፡፡
ከዚሁ ጥቃት ጋር በተያያዘ በድሬዳዋ ከተማ አንዲት እናት እና አራት ልጆቿን ጨምሮ 14 ሰዎች መገደላቸውን ከአካባቢው ለሰመጉ የደረሰው መረጃ ያመለክታል። አሁንም ይህ ሪፖርት በሚጠናቀርበት ጊዜ ከፍተኛ ውጥረት በድሬዳዋ ከተማ ታይዋንና አሸዋ ሰፈር በሚባሉ አካባቢዎች ነግሷል የንግድ ሱቆችም ተዘግተዋል።

ይህን አሳዛኝና ኢሰብዓዊ ድርጊት ሰመጉ በጥብቅ እያወገዘ በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ዜጐች ቤተሰቦች ፣ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ እና ቤት ንብረታቸውን ለወደመባቸው ዜጐች መፅናናትን ይመኛል፡፡ ሰመጉ በጥቃቱ የደረሰውን የጉዳት መጠን መርምሮ ይፋ እንደሚያደርግ እየገለፀ፤ የዜጐቹን ደህንነት የመጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት በመስጠት የድርጊቱን ፈፃሚዎችና አስፈፃሚዎች በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፤ የህዝቡን ፍላጐት መሠረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግ ጥሪውን ያቀርባል። መላው ህብረተሰብም ከመንግስት ጋር በመተባበር የመፍትሔው አካል እንዲሆን ሰመጉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

በመጨረሻም የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ህግን ለማስከበርና ስርዓትን ለማስፈን የሚወስዱት እርምጃ በከፍተኛ ጥንቃቄና የሀላፊነት ስሜት እንዲሁም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባከበረ መልኩ እንዲሆን ሰመጉ ያሳስባል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ ፒዲኤፍ

ሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ፀረ-ስቃይ ድርጅት (OMCT) አባል እና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡

144ኛ ልዩ መግለጫ – በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ሰብአዊ መብትች ጉባኤ ልዩ መግለጫውን ይፋ አድርጓል። በሰብአዊ መብቶች ጉባኤ 144ኛ ልዩ መግለጫ የሰብዓዊ መብቶ ጥሰቶ የተፈጸሙት ከጥር 2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 2010 ዓ.ም ባሉት 12ወራት ሲሆን ሪፖርቱ በዜጎች ላይ የተፈፀመ ግድያን፣ አስገድዶ መድፈርን እና መጠኑ የሰፋ የዜጎች መፈናቀልን አካቷል።

ይህ ሪፖርት ሁለት ክፍል ያለው ሲሆን በመጀመያው ክፍል የሶማሊ ክልል ልዩ ሀይል እና የመከላከያ ሰራዊት የፈፀሙት ጥቃት አንደሆነ ሪፖርቱ አካቷል። በምእራብ ሀረርጌ ዞን እና በባሌ ዞን ከሶማሊ ክልል ጋር በሚገኙ አዋሳኝ ቦታዎች የሶማሊ ክልል ሌዩ ሀይልና መከላከያ ሰራዊት በፈፀመው ጥቃት በምእራብ ሃረርጌ ዞን 160 ዜጎች ሲገደሉ በባሌ ዞን 96 ዜጎች ተገድለዋል፤ ይህኛው የሪፖርቱ ክፍል ጉዳት የደረሰባቸውንና የሟቾችን ስም ዝርዝር ይዞ የወጣ ሲሆን አስገድዶ መድፈርን እና የዜጎች መፈናቀልን አካቷል።

የልዩ መግለጫው ሁለተኛ ክፍል በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ በተነሱ ግጭትና ጥቃቶች ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ የሶማሌ ብሔረሰብ ተወላጆችን ስም ዝርዝር ያካተተ ሲሆን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን በተገኘ ሪፖርትና የሰመጉ ባለሙያዎች ቦታው ድረስ በመሄድ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦችና  ከአይን እማኞች ባጣሩት መሰረት ሪፖርቱ በሸፈናቸው 12 ወራት ውስጥ በተፈፀመ ጥቃት 451 ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ቁጥሩ የበዛ የዜጎች መፈናቀል፤ መደፈር እና የአካል ጉዳት በዚሁ ክፍል ተካቷል።

የሰመጉ 144ኛ ልዩ መግለጫ ሙሉውን ሪፖርት እዚህ ያገኛሉ

ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር ሕዝብ ተስፋ የጣለበት አጋጣሚ እንዳይባክን!

ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም – ከሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ። መሉ መግለጫውን እዚህ  (ፒዲኤፍ) በመጫን ማውረድ የችላሉ።

 

 

መንግስት ለሰላም፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለዲሞክራሲ መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳይ!!

መንግስት ለሰላም፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር እና ለዲሞክራሲ መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያሳይ ሰመጉ ጠየቀ። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሔደው ስብሰባ የፖለቲካ ምሕዳሩ መጥበቡን፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በየቦታው እንደሚታዩ እና ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር መንግስት ተገቢውን ጥረት አለማድረጉን በመገምገም የገዢው ፓርቲ አመራር ኃላፊነቱን እንደሚወስድ በመግለፅ ፓርቲው መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል።   የግንባሩ አባል ድርጅቶችም ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓም  በሰጡት መግለጫ ይህንን በድጋሚ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

ሰመጉ ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓም ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስት ለመውሰድ ቃል የገባቸው እርምጃዎች በመልካም ጐኑ የተመለከተ ሲሆን በዘላቂነት ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በሃገሪቱ ለመገንባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የህግ፣ የተቋማትና የአሰራር ማሻሻዮችን ማድረግ እንዳለበት ሰመጉ አሳስቧል።

ሙሉ መግለጫውን እዚህ ያግኙ  HRCO PR Jan 5 2018

በኢትዮጵያ ለብሔረሰብ ተኮር ጥቃቶችና ግጭቶች የማያዳግም የፖሊሲና የአፈጻጸም መፍትሄ ይሰጥ!

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት በጌዴኦ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እና በሐረሪ ክልላዊ መንግስት በሐረር ከተማ ውስጥ እየተፈፀሙ ያሉ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ሰመጉ) መንግስት ለብሔረሰብ ተኮር ጥቃቶች የማያዳግም የፖሊሲና የአፈፃፀም መፍትሔ እንዲሰጥ ጠየቀ። ሰመጉ በ143ኛ ልዩ መግለጫው በኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ግጭቶች እጅጉን ተባብሰው መቀጠላቸውንና አሳሳቢ ቀውስና መዘዝ በማስከተል ላይ መሆናቸውን ገልጿል። መግለጫው በጌዴኦ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የብሔረሰቡ ተወላጅ ባልሆኑ ዜጐች ላይ የተፈጸመውን ግድያ፣ ድብደባ፣ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ቃጠሎ በዝርዝር አካቷል። በተጨማሪም በሐረሪ ክልል የአፍረንቀሎ የኦሮሞ ባህልና ታሪክ ማዕከልን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ መጣልን ተከትሎ በኦሮሞ ማሕበረሰብ ወጣቶች ላይ የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችንም ይፋ አድርጓል።

መንግስት ከብሔር ጋር ለተያያዙ ጥቃቶች እና ግጭቶች በቂ ትኩረት ባለመስጠቱ የበርካታ ዜጐች ህይወት መጥፋቱን፣ አካል መጉደሉን፣ በመቶ ሺዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ መገደዳቸውን አስታውሶ፤ ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የመንግስት ባለሥልጣናት ራሳቸውን እንዲመለከቱ እና ህዝብን ከህዝብ ከሚያጋጭና ሐገርን ከሚጐዳ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሰመጉ ጠይቋል። መንግሥትም ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሰጥቶ ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲፈልግለት አሳስቧል፡

ሙሉ መግለጫውን እዚህ ያግኙ