በአዲስ አበባ ለተፈፀመው ጅምላ እሥራት መንግስት በቂ ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል – መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም

መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሔደው ጅምላ እስር ከመንግስት ሙሉ ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በሰጡት መግለጫ ባለፈው ሳምንት በመዲናችን በተካሔደው የጅምላ እስር በከተማዋ በነበረው (ሁከት) ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል ያላቸውን 1,204 ዜጉችን ጨምሮ፤ ከጫት ቤት፣ ከሺሻ ቤትና ከቁማር ቤት በገፍ ያፈሳቸውን በአጠቃላይ ወደ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ዜጐችን ማሰሩን ገልፀዋል።

ምንም እንኳን ፖሊስ ከተማዋን ለማረጋጋት እርምጃ መውሰዱ ተገቢ ቢሆንም ከሕግ አግባብ ውጪ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መጠነ_ሰፊ እስር መፈፀሙ፣ ጅምላ እስራቱ ሠላማዊ ዜጐችንም ጭምር ዒላማ ማድረጉ፣ ጥቂት የማይባሉ ታሳሪዎች ላይ ፖሊስ ድብደባ መፈፀሙ፣ ብሎም ዘላቂ የአካል ጉዳት ማድረሱ፣ በሕግ ወንጀል እንደሆነ በግልፅ ባልተደነገጉ ሥፍራዎች ያገኛቸውን ዜጐች ማሠሩ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ እስራቶቹ መፈፀማቸው፣ እንዲሁም ሠላማዊውን ሕዝብ ጭንቀት ውስጥ በከተተ መልኩ ግልፀኝነት በጐደለው ሁኔታ የጅምላ እስሩን መነሻ ምክንያት እና የታሳሪዎችን እጣ ፈንታ በፍጥነት ለሕዝብ ይፋ አለማድረጉ የፖሊስን እርምጃ ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው።

ሰመጉ ያነጋገራቸው የእስሩ ገፈት የቀመሱ ዜጐች ፖሊስ በምርመራ ወቅት የተቀናቃኝ ፓርቲዎች አመራሮች ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የአቀባበል ዝግጅቱን ለምን አስተባበራችሁ፣ ለምን የፓርቲዎቹ ደጋፊ ሆናችሁ የሚሉና ተመሳሳይ የምርመራ ጥያቄዎች እንደቀረቡላቸው ለሰመጉ አስረድተዋል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎችን እና ከቡራዩ ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ ሲያስተባብሩ የነበሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች በብዛት መታሠራቸውን ስንመለከት፣ ፖሊስ የሰጠውን “ሁከትን የማረጋጋት“ ምክንያት ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሁከቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበሩ ያላቸውን 1,204 ዜጐች ለተሃድሶ ስልጠና በሚል ምክንያት ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ መውሰዱንም አረጋግጧል፡፡ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው በግልፅ ቢደነግግም ፖሊስ ይህንን የታሳሪዎች ህገ-መንግስታዊ መብት በመጣስ ካለፍርድ እና ገደቡ ለማይታወቅ ግዜ ታሳሪዎችን ወድ ወታደራዊ ካምፕ ወሰዷል፡፡ ፖሊስ ታሳሪዎቹን በመደበኛ ፖሊስ ጣቢያዎች ለማቆየት ያልቻለበትንም ምክንያት ግልፅ አላደረገም፡፡ ይህ የፖሊስ ድርጊት የዜጐችን ሕገ መንግስታዊ መብት በግልፅ የጣሰ በመሆኑ ከሕግ አግባብ ውጪ የተያዙ፣ ክስ ሳይቀርብባቸው ወይም ሳይፈረድባችው የታሰሩ ዜጐች እንዲፈቱ ሰመጉ ይጠይቃል፡፡

ሀገሪቱ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውስጥ በነበረችበት ወቅት በተለያዩ ወታደራዊ ካምፖች ታስረው የነበሩ ዜጐች ይደርስባቸው የነበረውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ትውስታ ከአእምሮ ባልጠፋበት በዚህ ወቅት ለስልጠና በሚል ሠበብ መንግስት ዜጐችን ወደ ወታደራዊ ካምፕ ማጋዙ ለሌላ ዙር መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳያጋልጣቸው ሰመጉ ይሰጋል፡፡ በመሆኑም በሁከት እና በግርግር ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ዜጐች ሰብዓዊ መብታችውን በጠበቀ መልኩ የመያዝ መብታችው እንዲከበር፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በወዳጀቻቸው እና በሕግ አማካሪዎቻቸው የመጐብኘት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው፤ እንዲሁም ክስ ያልተመሠረተባቸው ዜጐች በፍጥነት እንዲለቀቁ ሰመጉ ይጠይቃል፡፡

መግለጫውን በፒዲኤፍ እዚህ ያገኛሉ።

 

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ)፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀጽ 1(ሀ) እና በኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር ከ404-482 በተጻፉት ድንጋጌዎች መሠረት መስከረም 29 ቀን 1984 ዓ.ም. በአባላት የተመሠረተ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ነው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

*

*