በሐገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ከምን ጊዜውም የበለጠ ጥረት ለማድረግ ቃላችንን በድጋሚ እናጸናለን!!!

hrco-25-yearsየሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ)፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀጽ 1(ሀ) እና በኢትዮጵያ ፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር ከ404-482 በተጻፉት ድንጋጌዎች መሠረት መስከረም 29 ቀን 1984 ዓ.ም. በአባላት የተመሠረተ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ነው፡፡ ሰመጉ በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ዐዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት “ኢትዮጵያዊ የበጎ አድራጎት ማኅበር” ሆኖ በምዝገባ ቁጥር 1146 በሕጋዊነት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ ሰመጉ ከማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሃይማኖት ተቋም፣ የብሔረሰብ ቡድን፣ ማኅበራዊ መደብ ወዘተ የማይወግን፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ነጻና ገለልተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተከላካይ ተቋም ነው፡፡ ሰመጉ የቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት፣ ለሕግ የበላይነት መስፈንና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ነው፡፡ ሰመጉ ላለፉት 25 ዓመታት በቆመላቸው ዐበይት ዓላማዎች ላይ በመመርኮዝ፣ ሁለንተናዊ ሐገራዊና ሕዝባዊ ተልዕኮ በመያዝ በነደፋቸው በርካታ የመርሐ-ግብር ተግባራት አማካኝነት ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እና ሕጋዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

ዓበይት ዓላማዎቹንና ተልዕኮውን ለማሳካት ሰመጉ ፈርጀ ብዙ የሆኑ የመርሐ ግብር ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትና ለሕዝብ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ሥልጠና መስጠት ነው፡፡ የመንግሥት አካላት በዋነኛነት የግዴታዎች ተሸካሚ፣ ሕዝብም በዋነኛነት የመብቶች ባለቤት እንደመሆናቸው መጠን፣ የመንግሥት አካላትም መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታቸውን በዕውቀት፣ በችሎታና በጽኑ ዕምነት ላይ ተመርኩዘው እንዲወጡ፣ ሕዝብም እንዲሁ በዕውቀት፣ በችሎታና በጽኑ ዕምነት ላይ ተመርኩዞ መብቱን እንዲያስከብር ሰመጉ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ሥልጠና ይሰጣል፡፡

የሰመጉ መለያውና ግንባር  ቀደም ተግባሩ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝና ሁኔታ መከታተል፣ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ማጣራትና በማስረጃ የተደገፉ መግለጫዎችን ማውጣት ነው፡፡ ሰመጉ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎች ፍትሕና ካሣ እንዲያገኙ፣ የጥሰት ፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁና ወንጀል ሠርቶ በነጻ መሄድ እንዲያበቃ፣ ከእያንዳንዱ ክስተት ትምህርት ተወስዶ ለወደፊቱ ጥንቃቄና እርማት እንዲደረግ ሲጮኽና ሲጠይቅ ቆይቷል፣ አሁንም በመጠየቅ ላይ ነው፤ ለወደፊትም በዚሁ ይቀጥላል፡፡

በተጨማሪም በተለይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሰለባ ለሆኑ ዜጎች የተለያየ ደረጃና መልክ ያለው የሕግ ድጋፍ መስጠት፣ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወንና ውጤቶቹን በስብሰባዎችና በልዩ ልዩ የመገናኛ መንገዶች ማሠራጨትና የአድቮኬሲ ሥራዎችን መሥራት፣ በመንግሥት የወጡና የሚወጡ ሕጎች ይዘትና አፈጻጸማቸውን መከታተል፣ የሕግ ታራሚዎችን መጎብኘትና ሰብዓዊ መብቶቻቸው መጠበቃቸውን መከታተልና የፍርድ ሂደት መከታተል  የሰመጉ ዋና ዋና ተግባራት ናቸው፡፡

በእስካሁኑ ቆይታው ሰመጉ 36 መደበኛ መግለጫዎችና 141 ልዩ መግለጫዎችን በተጨማሪም በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ ሰመጉ አሁን በሚገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም ቢሆን፣ ሁኔታና ዐቅም በፈቀደለት መጠን የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ የሕግ የበላይነትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ካለው የጸና ዓላማ አኳያ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ድርጅታችን ላለፉት 25 ዓመታት ይህን ሁሉ ሥራ ሲያከናውን የቆየው ግን ያለችግር አልነበረም፡፡ በመብቱ ባለቤት ሕዝብ በኩልም ሆነ በግዴታ ተሸካሚው መንግሥት በኩል የሰብዓዊ መብት ግንዛቤውና ቁርጠኝነቱ በሚገባው መጠን ባልዳበረበት ደረጃ ላይ ከመሆኑ አንፃር በየጊዜው የሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግሥት በኩል ለድርጅቱ የነበረውና አሁንም ያለው ተገቢ ያልሆነ አተያይ እና በአጠቃላይ በሲቪል ማኅበረሰቡ ላይ የወሰዳቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች የድርጅቱን ሕልውና ጭምር የሚፈታተኑ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት በተለያየ ጊዜ ድርጅቱን ሲመሩ የነበሩ ግንባር ቀደሞችን ጨምሮ በርካታ አባሎቻችንና ሠራተኞቻችን በተለያዩ ጊዜያት ታሥረው ተፈትተዋል፣ ዛሬም ታሥረው የሚገኙ አባሎቻችን አሉ፤ አሰፋ ማሩ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍሏል፤ ጥቂት የማይባሉ መሪዎቻችን፣ አባሎቻችንና ሠራተኞቻችን ከአገር ተሰድደዋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በበኩላቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ ‹‹ድርጅቱን መጠጋትም ሆነ ከድርጅቱ ጋር ተባብሮ መሥራት ዋጋ የሚያስከፍል ነው›› ተብሎ እንዲታሰብና ድርጅቱን ለመሸሽ ምክንያት ሆነዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ድርጅቱ በአገሪቱ ሕግ መሠረት የተቋቋመ፣ በአገሪቱ ሕግ የሚተዳደር የሰብዓዊ መብት ተቋም መሆኑ እየታወቀ መንግሥት ድርጅቱ ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን ቀርቦ ከማየትና ዓላማውንም በቅንነት ከመረዳት ይልቅ ለድርጅቱ ተገቢ ያልሆነ ግንዛቤ መያዙና አንዳንዴም የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ እንደሚሠራ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መቁጠሩና ማስቆጠሩ በድርጅቱ ሥራ ላይ ከፍተኛ ሳንካ ሆኖ ቆይቷል፡፡

መንግሥት በ2001ዓ.ም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበራት እንዲመዘገቡና አዲስ ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኙ የሚያስገድደውን ዐዋጅ ቁጥር 621/2001 ዐውጇል፡፡ መንግሥት ዐዋጁን ያወጣሁት ማኅበራቱ በሕዝብ ስም የሚሰበስቡትን ገንዘብ በትክክል ለሕዝቡ ጥቅም እንዲያውሉት ለማስቻል ነው በሚል ቢከራከርም በተለይ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ አገር በቀል ድርጅቶች ከበጀታቸው ከ10 በመቶ በላይ ከውጭ አገር የገንዘብ ምንጭ እንዳይቀበሉ መከልከሉ ድርጅታችንን ጨምሮ በርካታ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ አገር በቀል ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፤ ጥቂት የማይባሉ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችንም ከዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች-ተኮር ሥራ እንዲገለሉ አስገድዷቸዋል፡፡

የዐዋጁን መውጣት ተከትሎ፣ ኢሰመጉ/ሰመጉ ዐዋጁ ከመውጣቱ በፊት ከአባላትና ከአገር ውጭ ምንጮች በስጦታና በዕርዳታ አሰባስቦት የነበረው ከስምንት ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ በመንግሥት ታግዷል፡፡ ይኸው በባንክ የነበረ የሰመጉ ሀብት በመታገዱና ከ10 በመቶ በላይ ከውጭ ምንጭ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት መከልከሉ፣ በተለይ ለሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ድጋፍ ማድረግ ባልተለመደበትና በሚያስፈራባት ሐገራችን ውስጥ ሰመጉ በከፍተኛ የገንዘብ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ፕሮግራሞቹን ለማጠፍ ተገድዷል፡፡ በአንድ ጊዜ ከ50 በላይ ሠራተኞቹን ለማሰናበትና ስምንት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹን ለመዝጋት ተገድዷል፤ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራን ጨምሮ፤ በልዩ ልዩ የሰብዓዊ መብቶች ሥራዎቹ ይሸፍናቸው ከነበሩ የሐገራችን አካባቢዎች ለመራቅ ተገዷል፤ በርካታ ፕሮግራሞቹን አጥፏል፡፡ በተጨማሪም አዋጁ ባደረሰብን የአቅም ጉዳት ሳቢያ በአገሪቷ ከ3 ክልሎች በላይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቻችንን ይዘን ለመቆየት አልቻልንም፡፡ በሌላ በኩል አዋጁ አንድ ድርጅት ከመጠሪያ ስሙ ፊት “የኢትዮጵያ” የሚል ቅጥያ ለመያዝ በሐገሪቱ በ5 የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ጽ/ቤቶች ሊኖሩት እንደሚገባ ደንግጓል፤ በዚህ የዐዋጁ ድንጋጌ መሠረት  ‹‹የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ›› በሚል ስንጠራበት ከነበረው ሥያሜያችን ላይ ‹‹የኢትዮጵያ›› የሚለውን በመቀነስ ‹‹የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ›› በሚል ሥያሜ እንድንወሰን ተገድደናል፡፡

በአዋጁ ማግሥት ሰመጉ የዳግም ምዝገባ ጥያቄ ባቀረበበት ጊዜም፣ ምርጫ መታዘብን ጨምሮ ከምርጫ ጋር የተያያዙ የመርሐ ግብር ተግባራትን ከመተዳደሪያ ደንቡ ካላሰወጣ በስተቀር በድጋሚ መመዝገብ እንደማይችል በቁርጥ በተገለጸለት መሠረት ሰመጉ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ተግባራቱን ሁሉ ለማቋረጥ ተገዷል፡፡ በመሆኑም ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ሰመጉ የመራጮች ትምህርት አልሰጠም፤ ምርጫዎችንም አልታዘበም፡፡

በዚህ አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የገለጽናቸውንና ልንገልጻቸው ያልቻልናቸውን በርካታ ችግሮች አልፈን እነሆ ዛሬ ድርጅቱ ከተመሠረተ 25ኛ ዓመታችን ላይ ደርሰናል፡፡ ልደትን ማክበር የተለመደ ነውና እኛም የድርጅታችንን 25ኛ ዓመት የልደት በዓል ለማክበር እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ እንኳንስ አሁን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች (መንግሥት ሁሉ እያመነ እንደሚገኘው) ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄ አንሥተው አደባባይ እየወጡ ባሉ ዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሶ እያለ ይቅርና በድርጅታችን ላይ ሲደርስ ከነበረው ጫና አንፃር እንኳን የምሥረታ በዓላችንን በፈንጠዝያ ለማክበር እንደማናስብና እንዳልተዘጋጀንም ለመገመት አያዳግትም፡፡

ይልቁንም በዓላችንን የምናከብረው ‹‹ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም›› በሚል መሪ ቃል ሥር በአገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ከምን ጊዜውም የበለጠ ጥረት ለማድረግ ቃላችንን በድጋሚ በማጽናት ነው፡፡ ለዚህም ቃላችን ምስክር ይሆነን ዘንድ የድርጅቱን የገንዘብ ዐቅም በማጠናከር፣ የአገልግሎት አድማሱንና ተደራሽነቱን ለማስፋትና ሥራውንም ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል በማሰብ ከመስከረም 29 ቀን 2009ዓ.ም ጀምሮ የሚከናወኑ የተለያዩ የበዓል አከባበርና የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን አዘጋጅተናል፡፡ በዚህም መሠረት የድርጅቱ ሠራተኞችና አባላት የሚሳተፉበት የእግር ጉዞ በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ይደረጋል፣ በወቅታዊ የሐገራችን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታዎች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል፣ የገቢ ማሰባሰቢያ የምሳ ዝግጅትና በዚሁ ዝግጅት ላይ የሥዕል ሥራዎች ለጨረታ የሚቀርቡበት ሥነ ሥርዓት ይኖረናል፤ የሰመጉ ዓርማና መሪ ቃል የታተመባቸው ሸሚዞችና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ለሽያጭ ይቀርባሉ፡፡ ዝግጅቶቻችን ስለሚከናወኑባቸው ቀናትና ቦታዎች በየጊዜው አግባብ ባለው መንገድ ለሰመጉ ደጋፊዎችና ለሰብዓዊ መብት ቤተሰቦች ሁሉ እናሳውቃለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ መንግሥት በሐገራችን ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ለምናደርገው ሰብዓዊና የዜግነት ጥረታችን ተገቢውን ዕውቅና እንዲሰጥ፣ ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር መብታችንን ሙሉ በሙሉ እንዲያከብርና እንዲያስከብርልን፣ ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ እንዲያደርግልን፣ በባንክ የተያዘው ገንዘባችንን እንዲመልስልን፣ አላሰራ ያለንን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት አዋጅ በሚያሰራ መልኩ እንዲያሻሽልና ከማግለል ይልቅ በመቀራረብ፣ በዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሠረት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግልን አበክረን እንጠይቃለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ፣ በሐገር ውስጥም ሆነ ከሐገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪዎች በተለይ ከጎናችን እንድትቆሙና ጥረታችንን በተቻላችሁ ዓይነት፣ መልክና መጠን እንድትደግፉ ሰብዓዊና ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

 

‹‹ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

*

*