የሰዎች በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት ያለሥጋት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብታቸው ይከበር! ጥቅምት 07 ቀን 2012 ዓ/ም

የሰዎች በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት ያለሥጋት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብታቸው ይከበር! ጥቅምት 07 ቀን 2012 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ /ኢሰመጉ/ ለሕግ ልዕልና፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የቆመ ድርጅት ነው። በመሆኑም በአገሪቱ በየጊዜው የሚከሰቱትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቷቸው መፍትሄ እንዲገኝላቸው ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከማሳሰብ የተቆጠበበት ጊዜ የለም።
የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ክፍል 2 አንቀፅ 32(1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር መብት እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ ክፍል አንድ አንቀጽ 14 እና ክፍል 2 አንቀፅ 29 (1) እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈር የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት አለው፣ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል። እንዲሁም ይህ ነጻነት ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነጻነቶችን እንደሚያካትት በሕገ መንግሥቱ ሠፍሯል።
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 30(1) ለማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብትን አጎናጽፏል። ኢትዮጵያ የተቀበለችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀፅ 19 ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራሱ አስተያየት ሊኖረውና አስተያየቱን የመግለፅ መብት፣ እንዲሁም በዚሁ ቃል ኪዳን አንቀፅ 21 ማንኛውም ሰው ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግ መብት እንዳለው በመግለጽ ይህንንም መብት የቃል ኪዳኑ ፈራሚ ሐገራት እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ ያስገድዳል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የአፍሪካ የግለሰብና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀፅ 11 ማንኛውም ሰው ሐሳቡን ለመግለጽ በነጻነት መሰብሰብ እንደሚችል በመግለጽ እነዚህንም መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና መብቶቹ የሚከበሩባቸውን ሁኔታዎች የማሟላት ግዴታ በአባል ሐገራት ላይ ይጥላል። እነዚህን የዜጎችን የአካል ደኅንነትና ነጻነት መብቶች የመጠበቅ ኃላፊነት በግንባር ቀደምትነት የተጣለበት መንግሥት ነው። ይሁንና እነዚህ ሐገራዊ፣ አሕጉራዊና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ባለመከበራቸው ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።
ከመስከረም 17 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ በጎንደርና በጭልጋ አካባቢ በደረሰ የጸጥታ ችግር ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሞትና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህ መግለጫ ይፋ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ በአካባቢው መለስተኛ መረጋጋት የታየ ቢሆንም ከአዘዞ በጭልጋ ወደ መተማ በሚወስደው መሥመር ላይ ባለው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ምክንያት ተሽከርካሪዎች ያለ የጸጥታ ኃይሎች አጃቢነት ለመንቀሳቀስ አልቻሉም። ዜጎችም ወደፈለጉበት አካባቢ ለመንቀሳቀስና ምርቶቻቸውን ለመገበያየት አልቻሉም። መንግሥት የአካባቢውን ችግር በማጥናት ዘለቄታዊ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም በግጭቱ የተሳተፉ አካላት ተለይተው ለሕግ ሊቀርቡ ይገባል።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ ከተማና አካባቢው ከመስከረም 24 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ የታጠቁ ኃይሎች ተራራ ላይ ሆነው ወደ ሰዎች መኖሪያና የእርሻ ማሳ ተኩስ በመክፈት በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው ከስድስት የሚበልጥ ሰዎች ተገድለዋል፣ ከስምንት የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አርሶ አደሮችም የደረሰ ምርታቸውን ለመሰብሰብ አልቻሉም። ለሦስት ቀናት ባንኮች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት ተዘግተው ቆይተዋል። አሁንም ሕዝቡ በሥጋት ላይ ይገኛል። ለዚህ ተደጋግሞ ለሚነሳ ችግር መንግሥት ሰፊ ጥናት በማድረግ ድርጊቱን የፈጸሙ ኃይሎች በአስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡና ለወደፊቱም የዜጎችን በሰላም ያለ ሥጋት የመኖር መብት እንዲያስጠብቅ ኢሰመጉ ይጠይቃል።

ዜጎች ለሥራ፣ ለትምህርት፣ ለንግድና ለተለያዩ ጉዳዮች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው እየተጣሰ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ትብብር ጭምር መንገድ እየተዘጋ ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል። በ01/02/12 ዓ/ም ከጎንደር፣ ከባሕርዳርና ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ በጉዞ ላይ እንዳሉ በኦሮሚያ ክልል ጎሐጽዮን ከተማ ሲደርሱ ‹‹ወደ አዲስ አበባ ማለፍ አትችሉም›› ተብለው ከ80 በላይ መኪናዎች እንዲመለሱ ተደርገዋል። በማግስቱም ግማሽ ቀን ድረስ መንገዱ ተዘግቶ ቆይቷል። በዚሁ ምክንያት ተሳፋሪዎች ከፍተኛ መጉላላት ደርሶባቸዋል። ጉዟቸው የተስተጓጎለባቸው ዜጎች ለምግብ፣ ለውኃና ለመኝታ አገልግሎቶች ዕጦት ተዳርገዋል። በተጨማሪም በተለያዩ ቀናት በኦሮሚያ ክልል ሸኖና በኬ ከተማ የጸጥታ አካላት ባሉበት መንገድ ተዘግቶ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ አካባቢዎች ደብረብርሃንን አቋርጠው የሚሄዱ መኪናዎችና ተጓዦች ጉዟቸውን እንዳይቀጥሉ በአካባቢው ወጣቶች በመከልከላቸው በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ መጉላላት ተፈጽሟል፤ በአገር ኢኮኖሚም ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሏል። መንግሥት በሕገወጥ አካሄድ መንገድ በዘጉት አካሎች ላይ አስቸኳይ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ ካልወሰደ ወደፊትም ችግሩ እየተባባሰ ሄዶ ዜጎች ወደሚፈልጉት አካባቢ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው እየተገደበ ለሥጋት የሚጋለጡ ስለሆነ፣ ብሎም ለከፋ ችግርና አለመረጋጋት ስለሚዳርግ መንገዶቹ የተዘጉበትን ምክንያት በማጣራት ድርጊቱን በፈፀሙ፣ ባስፈፀሙና በተባበሩ ማናቸውም አካላት ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ በአፋጣኝ እንዲወሰድ ኢሰመጉ ይጠይቃል።
ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ባላደራ ምክር ቤት›› በመባል የሚጠራው አካል ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በ26/01/2012 ዓ.ም ለከተማው አስተዳደር አስታውቆ በዝግጅት ላይ ሳለ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ01/02/2012 ዓ.ም ተከልክሏል። የምክር ቤቱ አባላት እና ደጋፊዎች የሆኑ ቁጥራቸው ሐያ የሚሆኑ ወጣቶች በፖሊስ ተይዘው በተለያዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች ለሰዓታት ከቆዩ በኋላ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ተለቅቀዋል። እነዚህ የመብት ጥሰቶች ኢሰመጉን በእጅጉ ያሳስቡታል፤ በሐገራችን በጭላንጭል የሚታየውና በከፍተኛ ፈተና ውስጥ የሚገኘውን ጅምር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይበልጡኑ እንዳያጨልመው ያሠጉታል።
ከላይ ለተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች አስተዋጽኦ የሚያደርጉና በማኅበረሰባችን ውስጥ እየገነኑ የመጡት አክራሪ ብሔርተኝነት፣ የእርስበርስ አለመቻቻል እና ብሔርተኮር መድልዎ ከአገር አልፈው ለቀጠናው አሥጊ በመሆን ላይ ይገኛሉ። በአክራሪ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ምክንያት ግለሰቦች የጥቃት ዒላማ እየተደረጉ ናቸው፣ የዜጎች ንብረት እየተዘረፈና እየወደመ ነው። በቡራዩና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች አብሮ የመኖር ዋስትና ያሳጣሉ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋሉ። ቋንቋና ጎሣ የለየ ጥቃት በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን መስተጋብር በእጅጉ በመሸርሸር የሐገር ሕልውናን ሊያጠፋ ይችላል። ስለሆነም፣ በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸም ብሔር የለየ ጥቃትና መድልዎን መከላከል የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።
በአሁኑ ሰዓት ወጣቶች በየክልሉ የሚደራጁበት መንገድ እጅግ በሚያስደንግጥ ሁኔታ ብሔርን ብቻ መሠረት ያደረገ ሆኗል። ሕጋዊ ሰውነት ሳይኖራቸው በየሥፍራው የሚንቀሳቀሱ የወጣቶች ስብስቦች በቅርቡ በሐገራችን የተካሄደውን ፖሊቲካዊ ለውጥ በማምጣት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው የማይታበል ሐቅ ቢሆንም እነዚህ ብሔርን መሠረት ያደረጉ የወጣቶች ስብስቦች ለአደገኛ ፖሊቲካዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ ሲሆኑ እየታዘብን ነው። ከየአቅጣጫው የምንሰማው ብሔርን መሠረት ያደረገ ፕሮፓጋንዳና ይህንንም ወደ ተግባር ለመለወጥ በሚመስል መልኩ በየጎጡ ወጣቶች የሚደራጁበት መንገድ በሌሎች አገራት የተፈጸሙ የዘር ፍጅቶችን እንድናስታውስ የሚያስገድድ ነው።
በክልሎች፣ ዞኖች፣ ልዩ ዞኖችና ወረዳዎች የሚነሡ አስተዳደራዊ ቅሬታዎች የሚገለጹት በሥፍራው ለዘመናት በኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጅ ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ፣ በማፈናቀል፣ ሀብት ንብረት በመዝረፍና መንገድ በመዝጋት መልክ ከሆነ ሰንብቷል። በዚህ ሁሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ በድርጊት ፈጻሚነት ብዙውን ጊዜ የሚሳተፉት ሕጋዊ ሰውነት በሌላቸው ኢ-መደበኛ ቡድኖች የሚሰባሰቡ ወጣቶች ናቸው።
በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በስፋት የሚስተዋለው የአክራሪ ብሔርተኝነት አስተሳሰብና የወጣቶች ብሔርን መሠረት ባደረጉ ኢ-መደበኛ ቡድኖች መሰባሰብ በአስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ የሚዳርግ አደገኛ ውጤት እንዳያስከትል ያሠጋል። ሥጋቱ እውን እንዳይሆንና የወጣቶችንም ስብስቦች አዎንታዊ ማኅበራዊ ፋይዳ ወዳለው ሕጋዊ አደረጃጀት ለመለወጥ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ወጣቶች በሥራና በትምህርት ዕድል ማጣት ምክንያት ተስፋ ቆርጠው የእኩይ ፖሊቲከኞች ዓላማ ማስፈጸሚያ በመሆን በኹከት ተግባር ላይ ከመሠማራት የሚያቅባቸውን ፖሊሲ በመቅረፅ ተግባራዊ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። በመሆኑም፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ፖሊቲካዊ ቁርጠኛነቱ ኖሯቸው የዜጎችን ሕይወትና የአገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ የጅምላ ድርጊቶችን እንዲያስቆሙ፣ ዜጎችም በየአካባቢው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲቃወሙና ድርጊቶቹን እንዲከላከሉ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
ሁሉም መብቶች ለሁሉም! የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)

ኢሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ፀረ-ስቃይ ድርጅት (OMCT) አባልና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡

One thought on “የሰዎች በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት ያለሥጋት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብታቸው ይከበር! ጥቅምት 07 ቀን 2012 ዓ/ም

  1. አሉቴ ጀቤሶ

    የኢትዮጵያ የዜጎች ሰብአዊ መብት መፈተሽ አለበት ሰው ያለ አግባብ እየሞተና እየታሰረ ነው በነጻነት መንቀሳቀስ ዬለም ለምሳሌ
    በጉራጌ ዞን በቡታጅራ አከባቢ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

*

*