Latest Posts

Internship opportunity

Ethiopian Human Rights Council (EHRCO) was established on October 10, 1991, has since been legally undertaking it’s human rights monitoring, reporting, advocacy, research, legal aid and Human Rights  education activities across the country.

EHRCO is non- governmental, non-partisan, non-profit organisation that has no affiliation to any political party, religious institution, ethnic group, or social class. It’s sole objectives are to work for the respect of Human Rights, the Rule of the Law and the prvalence of Democracy in Ethiopia.  

Currently, EHRCO has registered under the Civil Society Organizations Proclamation number 1113/2019, with the registration number 1146 as a local organization.  

Opportunity;

The Human Rights Council (EHRCO) is looking for six Part-time Interns to work on our Election and related Human Rights Projects. A Minimal Stipend will be provided.

Requirements;

  • Law, International relation, political science – 3rd  year and above students and Masters students
  • Who can work 20 hours per week with office presence
  • Who has volunteerism experience and
  • Good communication skill with team mates

Interested and Qualified applicants can send updated CV, Cover Letter and School credentials to danethios@gmail.com or belen.ehrco@gmail.com until March 2, 2020.

”መልእክተ ኢሰመጉ” ወርኀዊ የበይነ መረብ መጽሔት ቅፅ —1 ቁር—1

መንግስት የዜጐችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣ!!

ኢሰመጉ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ
ETHIOPIAN HUMAN RIGHTS COUNCIL
ጋዜጣዊ መግለጫ
መንግስት የዜጐችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣ!!
ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ/ም


የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ክፍል አንድ አንቀፅ 14 ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሠሥ፣ በሕይወት የመኖር፣ የአካል
ደኅንነትና የነጻነት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት
ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን እንደማያጣ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 15 ላይ ሠፍሯል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 32(1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ
ወይም በሕጋዊ መንገድ ሐገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሐገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት መብት
እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ እንደዚሁም፣ አንቀፅ 40 (1) ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብት አጎናጽፏል፡፡
ኢትዮጵያ የተቀበለችውና የሕጓ አካል ያደረገችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀፅ 2 እያንዳንዱ ይህንን ቃልኪዳን
የተቀበለ አገር በግዛቱ ውስጥ ለሚኖርና በሥሩ ለሚተዳደር ማንኛውም ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም
ሌላ አመለካከት፣ በብሔራዊም ሆነ ማኅበራዊ አመጣጡ፣ በሀብት፣ በውልደት ወይም በሌላ መለኪያ ምንም ልዩነት ሳያደርግ በዚህ ሕግ ዕውቅና
ያገኙትን መብቶችና ነፃነቶች እንዲያስከብር ግዴታ ይጥላል፡፡ በተመሳሳይ፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የአፍሪካ የግለሰቦችና የሕዝቦች
መብቶች ቻርተር አንቀፅ 1 በሠነዱ ውስጥ የተጠቀሱትን መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና መብቶቹ የሚከበሩባቸውን ሁኔታዎች የማሟላት
ግዴታ ,በፈራሚ ሐገራት ላይ ይጥላል፡፡ እነዚህን የዜጎችን የአካል ደኅንነትና ነጻነት እንዲሁም የንብረት ባለቤትነት መብቶች የመጠበቅ ኃላፊነት
በግንባር ቀደምትነት የተጣለበት መንግሥት ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ ሐገራዊ፣ አሕጉራዊና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች
ባለመከበራቸው እና መንግስት የማስከበር ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡
 ከጥቅምት አንድ ቀን 2012ዓ.ም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እስከ ጥቅምት ሁለት ቀን 2012ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ አፋር ክልል
አፋምቦ ወረዳ ‹‹ሰንጋ›› በሚባል መንደር ከሌላ አካባቢ መምጣታቸው በተገለጸ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የ17 ሰዎች ሕይወት
ጠፍቷል፣ በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤
 ጥቅምት 11 ቀን 2012ዓ.ም ሌሊት አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ‹‹ጥበቃ እንዲያደርጉልኝ የተመደቡልኝ
የጸጥታ ኃይሎች ሊነሱብኝ ነው፡፡ ቤቴም በጸጥታ ኃይሎች ተከብቧል›› የሚል መልዕክት በማስተላለፋቸው መልዕክቱን የተቀበሉ
በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሌሊቱን ወደ ግለሰቡ መኖሪያ ቤት አምርተዋል፤ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎችም የአክቲቪስቱ
ደጋፊዎችና ተከታዮች በመሰባሰብ መንገድ ዘግተው የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ይህ የተቃውሞ ሠልፍ ወደ ግጭት አምርቶ
የበርካታ ዜጐች ሕይወት ጠፍቷል፣ በብዙዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ ግምቱ ያልታወቀ ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፣ የዜጐች
ያለሥጋት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቧል፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ የንግድ ድርጅቶችና
ት/ቤቶች ተዘግተዋል፡፡
ይህ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እስከሚሆንበት ሰዓት ድረስ ኢሰመጉ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ምንጮቹ በሰበሰበው መረጃ መሠረት
ግለሰቡ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ በተነሣው ተቃውሞና በተፈጸመው ብሔርና ሃማኖት ተኮር ጥቃት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በሐረር
ከተማ፣ በአወዳይ ከተማ፣ በድሬዳዋ ከተማ፣ በአዳማ፣ በባሌ ዞን ዶዶላ ወረዳ፣ በአምቦ ከተማ፣ በአርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ፣ በዝዋይ ከተማ፣ አርሲ
ነጌሌ፣ በባሌሮቤ በድምሩ ቁጥራቸው ከ67 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በርካታ የንግድ
ድርጅቶች መቃጠላቸውን፣ በብዙ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴና ተቋሞች ተዘግተው መዋላቸውን አረጋግጠናል፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ በርካቶቹ
ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በድንጋይ እና በዱላ ተወግረው መገደላቸው ሁኔታውን ይበልጥ አሰቃቂ አድርጐታል።
ኢሰመጉ የቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር፣ ለሕግ የበላይነት መስፈንና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ነው!!
EHRCO stands for Democracy, the rule of Law and the respect of Human Rights.
በተጠቀሱት ሥፍራዎች እና በሐገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ከሚፈጠሩ ሁከቶች ጋር ተያይዞ ብሔርን እና እምነትን መሠረት ያደረጉ
ጥቃቶችና ግጭቶች በዜጎች ላይ ሲፈጸሙ ተስተውለዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው ሁሉ የዞንና የወረዳ
አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የጸጥታ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ግዴታ ባለመወጣታቸውና በፍጥነት
ድርጊቶቹን ባለመቆጣጠራቸው ችግሩ በከፍተኛ መጠን ተባብሶ ወደ ከፍተኛ ቀውስ እያመራ ይገኛል። መንግሥት በተለይም ባለፉት ሁለት
ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች መሠል ድርጊቶች ሲፈጸሙ በዝምታ መመልከቱ፣ የድርጊቶቹን አነሳሾች እና ፈጻሚዎች በሕግ ፊት ተጠያቂ
ባለማድረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ክቡር ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ አካላቸው ጐድሏል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከመኖሪያ ቀዬአቸው
ተሰድደዋል፣ ዜጐች ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተዳርገዋል፣ የሕዝቡ ተቻችሎ እና ተከባብሮ የመኖር ዕሤቶችን እንዲሸረሸር አድርጓል።
ይህ መግለጫ በሚጠናቀርበት ወቅትም ዜጎችን ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች ዒላማ የሚያደርጉ መልዕክቶች
በማኅበራዊ ድረ ገጾች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።
በተጨማሪም፣ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ሮቤ እና በዶዶላ ወረዳዎች ለኢሰመጉ በስልክ በደረሰው መረጃ መሠረት አሁንም ተጨማሪ ጥቃት
ለመፈጸም በጥቃት አድራሾቹ እየተዛተባቸው እንደሚገኝ፤ በዚህም ምክንያት ለሕይወታቸው በመሥጋት ከአራት ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች
በሁለት አብያተ ክርስትያናት ተጠልለው እንደሚገኙና በርካቶችም በቤታቸው ውስጥ በፍርኀትና በጭንቀት የድረሱልን ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም፣ በድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖትንና ብሄርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በስፋት እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ይህ መግለጫ
በሚጠናቀርበት ወቅትም የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሥጋትና ፍርኀት ውስጥ እንደሚገኙ፣ ከሌላ የሐገሪቱ አካባቢዎች የመጡና ጥቃቱን
የሚፈጽሙ ወጣቶች የጦር መሣሪያዎች እና ድምፅ አልባ የስለት መሣሪያዎች የታጠቁ እንደሆኑ ከአካባቢው ለኢሰመጉ እየደረሱ ያሉ መረጃዎች
ያሳያሉ፡፡ የሐገር መከላከያ ሠራዊትም ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡
መንግሥት ለእነዚህም ሆነ ለተመሳሳይ ድርጊቶች ሕጋዊ እና የማያወላውል እርምጃ በመውሰድ የዜጐችን በሕይወት የመኖር፣ አካላዊ ደኅንነት
እና በፈለጉት የሐገሪቱ አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸውን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር ኢሰመጉ በድጋሚ ያሳስባል።
በተጨማሪም መንግሥት፡-
 በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች አማካይነት ዜጎችን ለጥቃትና ለግጭት የሚያጋልጡ ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያሠራጩ አካላትን
እንዲቆጣጠር፣
 ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ድርጊቱን ባነሣሡና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በፈጸሙ ግለሰቦችና አካላት እንዲሁም ይህንን
የመከላከልና የመቆጣጠር በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሳይወጡ በቀሩ የፀጥታ ኃይሎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ሕጋዊ
እርምጃ እንዲወስድ፣
 ጉዳዩ ተጣርቶ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ለሟች ቤተሰቦች፣ ቤት ንብረት ለወደመባቸውና ለተፈናቀሉ ዜጎች ካሣ እንዲከፍል
እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፍና ርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲያመቻች፣
 በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በስፋት የሚስተዋለው የአክራሪ ብሔርተኛነት አስተሳሰብን መሠረት ያደረጉ ኢ-መደበኛ ቡድኖች
እያደረሱ ያሉትን ጥፋት ለማስቆም የሚያስችል አስቸኳይ መፍትሄ በመስጠት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣
 በፌዴራል መንግሥት አካላትና በክልል መስተዳድሮች መካከል ያለው ግንኙነት ሕግን መሠረት ያደረገና የሕዝቦችን የጋራ
ተጠቃሚነት ያስከበረ መሆኑን እንዲያረጋግጥ፣
 በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ፖሊቲካዊ ቁርጠኛነቱ ኖሯቸው የዜጎችን ሕይወትና የአገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጋርጡ
የጅምላ የወንጀል ድርጊቶችን እንዲያስቆሙ፣
 ግለሰቦችም በተለያዩ ሚዲያ እየተሠራጩ የሚገኙትንና ሕዝብን ለግጭትና ለጥቃት የሚያነሣሡ ንግግሮችና የሐሰተኛ መረጃ
ከመፈብረክና ሳያመዛዝኑ ከማሠራጨት በመቆጠብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ፣ በየአካባቢው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች
ጥሰቶችን እንዲቃወሙና ድርጊቶቹን እንዲከላከሉ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ /ኢሰመጉ/ ለሕግ ልዕልና፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የቆመ ድርጅት
ነው፡፡
ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!

ኢሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች
ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ጸረ-ሥቃይ ድርጅት (OMCT) አባልና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ
መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ኅብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡


የሰዎች በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት ያለሥጋት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብታቸው ይከበር! ጥቅምት 07 ቀን 2012 ዓ/ም

የሰዎች በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት ያለሥጋት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብታቸው ይከበር! ጥቅምት 07 ቀን 2012 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ /ኢሰመጉ/ ለሕግ ልዕልና፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የቆመ ድርጅት ነው። በመሆኑም በአገሪቱ በየጊዜው የሚከሰቱትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቷቸው መፍትሄ እንዲገኝላቸው ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከማሳሰብ የተቆጠበበት ጊዜ የለም።
የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ክፍል 2 አንቀፅ 32(1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር መብት እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ ክፍል አንድ አንቀጽ 14 እና ክፍል 2 አንቀፅ 29 (1) እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈር የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት አለው፣ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል። እንዲሁም ይህ ነጻነት ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነጻነቶችን እንደሚያካትት በሕገ መንግሥቱ ሠፍሯል።
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 30(1) ለማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብትን አጎናጽፏል። ኢትዮጵያ የተቀበለችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀፅ 19 ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራሱ አስተያየት ሊኖረውና አስተያየቱን የመግለፅ መብት፣ እንዲሁም በዚሁ ቃል ኪዳን አንቀፅ 21 ማንኛውም ሰው ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግ መብት እንዳለው በመግለጽ ይህንንም መብት የቃል ኪዳኑ ፈራሚ ሐገራት እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ ያስገድዳል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የአፍሪካ የግለሰብና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀፅ 11 ማንኛውም ሰው ሐሳቡን ለመግለጽ በነጻነት መሰብሰብ እንደሚችል በመግለጽ እነዚህንም መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና መብቶቹ የሚከበሩባቸውን ሁኔታዎች የማሟላት ግዴታ በአባል ሐገራት ላይ ይጥላል። እነዚህን የዜጎችን የአካል ደኅንነትና ነጻነት መብቶች የመጠበቅ ኃላፊነት በግንባር ቀደምትነት የተጣለበት መንግሥት ነው። ይሁንና እነዚህ ሐገራዊ፣ አሕጉራዊና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ባለመከበራቸው ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።
ከመስከረም 17 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ በጎንደርና በጭልጋ አካባቢ በደረሰ የጸጥታ ችግር ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሞትና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህ መግለጫ ይፋ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ በአካባቢው መለስተኛ መረጋጋት የታየ ቢሆንም ከአዘዞ በጭልጋ ወደ መተማ በሚወስደው መሥመር ላይ ባለው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ምክንያት ተሽከርካሪዎች ያለ የጸጥታ ኃይሎች አጃቢነት ለመንቀሳቀስ አልቻሉም። ዜጎችም ወደፈለጉበት አካባቢ ለመንቀሳቀስና ምርቶቻቸውን ለመገበያየት አልቻሉም። መንግሥት የአካባቢውን ችግር በማጥናት ዘለቄታዊ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም በግጭቱ የተሳተፉ አካላት ተለይተው ለሕግ ሊቀርቡ ይገባል።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ ከተማና አካባቢው ከመስከረም 24 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ የታጠቁ ኃይሎች ተራራ ላይ ሆነው ወደ ሰዎች መኖሪያና የእርሻ ማሳ ተኩስ በመክፈት በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው ከስድስት የሚበልጥ ሰዎች ተገድለዋል፣ ከስምንት የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አርሶ አደሮችም የደረሰ ምርታቸውን ለመሰብሰብ አልቻሉም። ለሦስት ቀናት ባንኮች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት ተዘግተው ቆይተዋል። አሁንም ሕዝቡ በሥጋት ላይ ይገኛል። ለዚህ ተደጋግሞ ለሚነሳ ችግር መንግሥት ሰፊ ጥናት በማድረግ ድርጊቱን የፈጸሙ ኃይሎች በአስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡና ለወደፊቱም የዜጎችን በሰላም ያለ ሥጋት የመኖር መብት እንዲያስጠብቅ ኢሰመጉ ይጠይቃል።

ዜጎች ለሥራ፣ ለትምህርት፣ ለንግድና ለተለያዩ ጉዳዮች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው እየተጣሰ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ትብብር ጭምር መንገድ እየተዘጋ ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል። በ01/02/12 ዓ/ም ከጎንደር፣ ከባሕርዳርና ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ በጉዞ ላይ እንዳሉ በኦሮሚያ ክልል ጎሐጽዮን ከተማ ሲደርሱ ‹‹ወደ አዲስ አበባ ማለፍ አትችሉም›› ተብለው ከ80 በላይ መኪናዎች እንዲመለሱ ተደርገዋል። በማግስቱም ግማሽ ቀን ድረስ መንገዱ ተዘግቶ ቆይቷል። በዚሁ ምክንያት ተሳፋሪዎች ከፍተኛ መጉላላት ደርሶባቸዋል። ጉዟቸው የተስተጓጎለባቸው ዜጎች ለምግብ፣ ለውኃና ለመኝታ አገልግሎቶች ዕጦት ተዳርገዋል። በተጨማሪም በተለያዩ ቀናት በኦሮሚያ ክልል ሸኖና በኬ ከተማ የጸጥታ አካላት ባሉበት መንገድ ተዘግቶ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ አካባቢዎች ደብረብርሃንን አቋርጠው የሚሄዱ መኪናዎችና ተጓዦች ጉዟቸውን እንዳይቀጥሉ በአካባቢው ወጣቶች በመከልከላቸው በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ መጉላላት ተፈጽሟል፤ በአገር ኢኮኖሚም ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሏል። መንግሥት በሕገወጥ አካሄድ መንገድ በዘጉት አካሎች ላይ አስቸኳይ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ ካልወሰደ ወደፊትም ችግሩ እየተባባሰ ሄዶ ዜጎች ወደሚፈልጉት አካባቢ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው እየተገደበ ለሥጋት የሚጋለጡ ስለሆነ፣ ብሎም ለከፋ ችግርና አለመረጋጋት ስለሚዳርግ መንገዶቹ የተዘጉበትን ምክንያት በማጣራት ድርጊቱን በፈፀሙ፣ ባስፈፀሙና በተባበሩ ማናቸውም አካላት ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ በአፋጣኝ እንዲወሰድ ኢሰመጉ ይጠይቃል።
ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ባላደራ ምክር ቤት›› በመባል የሚጠራው አካል ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በ26/01/2012 ዓ.ም ለከተማው አስተዳደር አስታውቆ በዝግጅት ላይ ሳለ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ01/02/2012 ዓ.ም ተከልክሏል። የምክር ቤቱ አባላት እና ደጋፊዎች የሆኑ ቁጥራቸው ሐያ የሚሆኑ ወጣቶች በፖሊስ ተይዘው በተለያዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች ለሰዓታት ከቆዩ በኋላ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ተለቅቀዋል። እነዚህ የመብት ጥሰቶች ኢሰመጉን በእጅጉ ያሳስቡታል፤ በሐገራችን በጭላንጭል የሚታየውና በከፍተኛ ፈተና ውስጥ የሚገኘውን ጅምር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይበልጡኑ እንዳያጨልመው ያሠጉታል።
ከላይ ለተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች አስተዋጽኦ የሚያደርጉና በማኅበረሰባችን ውስጥ እየገነኑ የመጡት አክራሪ ብሔርተኝነት፣ የእርስበርስ አለመቻቻል እና ብሔርተኮር መድልዎ ከአገር አልፈው ለቀጠናው አሥጊ በመሆን ላይ ይገኛሉ። በአክራሪ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ምክንያት ግለሰቦች የጥቃት ዒላማ እየተደረጉ ናቸው፣ የዜጎች ንብረት እየተዘረፈና እየወደመ ነው። በቡራዩና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች አብሮ የመኖር ዋስትና ያሳጣሉ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋሉ። ቋንቋና ጎሣ የለየ ጥቃት በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን መስተጋብር በእጅጉ በመሸርሸር የሐገር ሕልውናን ሊያጠፋ ይችላል። ስለሆነም፣ በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸም ብሔር የለየ ጥቃትና መድልዎን መከላከል የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።
በአሁኑ ሰዓት ወጣቶች በየክልሉ የሚደራጁበት መንገድ እጅግ በሚያስደንግጥ ሁኔታ ብሔርን ብቻ መሠረት ያደረገ ሆኗል። ሕጋዊ ሰውነት ሳይኖራቸው በየሥፍራው የሚንቀሳቀሱ የወጣቶች ስብስቦች በቅርቡ በሐገራችን የተካሄደውን ፖሊቲካዊ ለውጥ በማምጣት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው የማይታበል ሐቅ ቢሆንም እነዚህ ብሔርን መሠረት ያደረጉ የወጣቶች ስብስቦች ለአደገኛ ፖሊቲካዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ ሲሆኑ እየታዘብን ነው። ከየአቅጣጫው የምንሰማው ብሔርን መሠረት ያደረገ ፕሮፓጋንዳና ይህንንም ወደ ተግባር ለመለወጥ በሚመስል መልኩ በየጎጡ ወጣቶች የሚደራጁበት መንገድ በሌሎች አገራት የተፈጸሙ የዘር ፍጅቶችን እንድናስታውስ የሚያስገድድ ነው።
በክልሎች፣ ዞኖች፣ ልዩ ዞኖችና ወረዳዎች የሚነሡ አስተዳደራዊ ቅሬታዎች የሚገለጹት በሥፍራው ለዘመናት በኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጅ ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ፣ በማፈናቀል፣ ሀብት ንብረት በመዝረፍና መንገድ በመዝጋት መልክ ከሆነ ሰንብቷል። በዚህ ሁሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ በድርጊት ፈጻሚነት ብዙውን ጊዜ የሚሳተፉት ሕጋዊ ሰውነት በሌላቸው ኢ-መደበኛ ቡድኖች የሚሰባሰቡ ወጣቶች ናቸው።
በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በስፋት የሚስተዋለው የአክራሪ ብሔርተኝነት አስተሳሰብና የወጣቶች ብሔርን መሠረት ባደረጉ ኢ-መደበኛ ቡድኖች መሰባሰብ በአስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ የሚዳርግ አደገኛ ውጤት እንዳያስከትል ያሠጋል። ሥጋቱ እውን እንዳይሆንና የወጣቶችንም ስብስቦች አዎንታዊ ማኅበራዊ ፋይዳ ወዳለው ሕጋዊ አደረጃጀት ለመለወጥ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ወጣቶች በሥራና በትምህርት ዕድል ማጣት ምክንያት ተስፋ ቆርጠው የእኩይ ፖሊቲከኞች ዓላማ ማስፈጸሚያ በመሆን በኹከት ተግባር ላይ ከመሠማራት የሚያቅባቸውን ፖሊሲ በመቅረፅ ተግባራዊ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። በመሆኑም፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ፖሊቲካዊ ቁርጠኛነቱ ኖሯቸው የዜጎችን ሕይወትና የአገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ የጅምላ ድርጊቶችን እንዲያስቆሙ፣ ዜጎችም በየአካባቢው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲቃወሙና ድርጊቶቹን እንዲከላከሉ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
ሁሉም መብቶች ለሁሉም! የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)

ኢሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ፀረ-ስቃይ ድርጅት (OMCT) አባልና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡