Latest Posts

የውይይት መድረክ

Happening_Now

ኢሰመጉ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።
ከዝግጅቶቹ ውስጥ በዛሬው እለት “የፍትህ አካላት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ላይ ያላቸው ሚና” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።
በውይይቱም ላይ የፍትህ ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እና ሚዲያዎች ተገኝተዋል።

በማናቸውም ወቅት ቢሆን፤ የሰላማዊ ሰዎች ደህንነት እና ሰብዓዊ መብቶችበሁሉም ወገኖች መከበር አለባቸው!ህዳር 07 ቀን 2013 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ – ኢሰመጉአስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ በማናቸውም ወቅት ቢሆን፤ የሰላማዊ ሰዎች ደህንነት እና ሰብዓዊ መብቶችበሁሉም ወገኖች መከበር አለባቸው! ህዳር 07 ቀን 2013 ዓ.ምየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ – ኢሰመጉ በትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው የጦርነት እንቅስቃሴ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ከፍተኛ አደጋ ላይ የጣለ መሆኑ ከፍተኛ ሥጋት አሳድሮበታል፡፡ ማንኛውም ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ያገኛቸው መብቶች በሰላማዊም ሆነ በጦርነት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ መሆናቸው የማይቀርና የሕግ ተጠያቂነትም ያለበት ነው፡፡ በመሆኑም፣ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች በጦርነቱ በቀጥታተሳታፊ ያልሆኑ እና ያልታጠቁ ንጹኃን ሰዎችን ደህንነት እና ሰብዓዊ መብቶች የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ኢሰመጉ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ በአካባቢው ያለው እንቅስቃሴ የሰላማዊ ሕዝብን የሕይወት እና አካላዊ ደህንነት አደጋ ላይ የማይጥል ሊሆን እንደሚገባው ማሳሰቡ አይዘነጋም፡፡ ሆኖም፣ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል፣ ማይካድራ ከተማ በግጭቱ ምንም ዓይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በስለታማ መሳሪያዎች ተወግተው እንደተገደሉ የኢሰመጉ የቅድመ-ምርመራ ግኝቶች አረጋግጠዋል፡፡ ይህን መሠሉ፣ ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጭፍጨፋ በማንም ይሁን፣ በምንም ምክንያት በፍጹምተቀባይነት የሌለው መሆኑን ኢሰመጉ ያስገነዝባል፡፡ኢሰመጉ፣ በዚህ ሰዓት የደረሰውን የጉዳት ዓይነት እና መጠን ለማጣራት በተቻለው አቅም ጥረት እያደረገ መሆኑን እየገለጸ፤ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ዳግም እንዳይፈጠር ሁሉም ወገኖች በከፍተኛ ትኩረት እንዲከታተሉ፣ እንቅስቃሴያቸው ኃላፊነት የተሞላበት እንዲሆን እና አጥፊዎችን ይዘው ለሕግ እንዲያቀርቡ ይጠይቃል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ በተለይም፣ በአላማጣ ከተማ ነዋሪ እናየሕግ እስረኞች የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ፣ አሁን ድረስ የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የማይታወቁ ሰዎች ደህንነት ኢሰመጉን በከፍተኛ ደረጃ አሳስቦታል፡፡ እንዲሁም ደግሞ፤ በግጭቱ በሁሉም ወገኖች ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት የአየር ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችሉ መሳሪያዎች በአብዝኃኛው የሰው ልጆች ብቻ ያላቸውን ሁኔታዎችን የማመዛዘን አዕምሯዊ ብቃት (human beings mental element) የሚያንሳቸው በመሆኑ፣ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችን እና የሲቪል ንብረቶችን የጥቃቱ ዒላማና ሰለባ እንዳያደርጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ ያስገነዝባል፡፡ማሳሰቢያ፡ትግራይ ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የዕለት እርዳታ የሚሹ ስደተኞች የተጠለሉበት ክልል እንደመሆኑ እና በግጭቱ ምክንያት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተፈናቀሉ ያሉ ሰዎች በመኖራቸው ለእነርሱ የሚደረጉት እንደ ምግብ፣ መድኃኒት እና ህክምና የመሳሰሉ ሰብዓዊ እርዳታዎች አቅርቦት እንዲረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ ኢሰመጉ ያሳስባል፡፡በግጭቱ ምክንያት ለቆሰሉ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችም ሊደረግ የሚገባው ሰብዓዊ ድጋፍ እና እርዳታም በተገቢው መንገድ እንዲረጋገጥ ያሳስባል፡፡ከወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሰዎች በብሔር ማንነታቸው ብቻ ተለይተው ለጥርጣሬ እና መድልዎ ተጋላጭ እየተደረጉ ስለመሆኑ የሚያሳዩ ምልክቶች በርካታ ናቸው፡፡ ለአብነት፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል የሚጓዙ መንገደኞች ከፓስፖርት በተጨማሪ የቀበሌ መታወቂያ እያሳዩ ለአድልዖ እየተጋለጡ መጠየቃቸው እና በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎች በብሔር ማንነታቸው ተለይተው እረፍት እንዲወጡ መደረጋቸው የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ አንጻር፤ የሕግ አስከባሪ አካላትም ሆነ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል፣ ሰዎች በብሔር ማንነታቸው ብቻ ተለይተው መድልዎ እንዳይደርስባቸው እና ለጥርጣሬ እንዳይዳረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግእንደሚኖርባቸው ኢሰመጉ ያሳስባል፡፡ኢሰመጉ ቀደም ሲልም አውጥቶት በነበረው መግለጫ እንዳሳሰበው፤ የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶችም ሆኑ ማንኛውም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ግጭትን የሚያባብሱ፣ ሰዎች በብሔር ማንነታቸው ብቻ ተለይተው ለጥርጣሬ እና መድልዎ ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርጉ፣ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሚሆኑ የሐሰት ዜናዎችን፣ የተሳሳቱ፣ የተዛቡ እና የተበከሉ መረጃዎችን ከመናገር፣ ከማባዛት እና ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ በድጋሚ ያሳስባል፡፡በመጨረሻም፤ ኢሰመጉ በትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ያለው የጦርነትእንቅስቃሴ ከዚህም የከፋ ሰብዓዊ ጉዳት እና ቁሳዊ ጥፋት ከማድረሱ በፊት፤ ሁሉም ወገኖች ችግሩን ሰላማዊ አማራጮችን ተጠቅመው የሚፈቱበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ በድጋሚ እያሳሰበ፤ ኢሰመጉም ሆነ መሰል የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በየጊዜው የሚያወጧቸውን ማሳሰቢያዎች እና ምክረ-ሐሳቦች የሚመለከታቸው የሕግ አውጪውም ሆነ የሕግ አስፈጻሚው አካላት፣ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት እና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጆሮ ሰጥተው፣ ፈጣን የመፍትሔ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያሳስባል፡፡

ህዳር 07 ቀን 2013 ዓ.ምአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የኢሰመጉ 29ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለ ኢሰመጉ መስራች ጉምቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም እና በቅርቡ ላጣናቸው የኢሰመጉ ባልደረባ እና አንጋፋ አባል የህሊና ጸሎት በማድረግ ተከፍቷል።አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም

ጠቅላላ ጉባኤ

የኢሰመጉ 29ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኤፌድሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የመሰብሰቢያ አዳራሽ: የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች፣ አባላት፣ የሁሉም ጽ/ቤት ሰራተኞች እና ኮሚቴዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም

ኢትዮጵያ፡በዘር ማጥፋት ወንጀል አፋፍ ላይ!


[147ኛ ልዩ የሰብዓዊ መብቶች ዘገባ]

ኢሰመጉ የቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር፣ ለሕግ የበላይነት መስፈንና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ነው!  

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ – ኢሰመጉ

ጋዜጣዊ መግለጫ

ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም          

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ – ኢሰመጉ በበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት ተመዝገቦ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚሠራ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በእስካሁኑ ቆይታው 38 መደበኛ የሰብዓዊ መብቶች ዘገባዎችን፣ 147 ልዩ ዘገባዎችን እና በልዩ በልዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ይፋ በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለሕዝብ ሲያሳውቅ ቆይቷል፡፡

በቅርብ ጊዜያት በሐገራችን ውስጥ እያጋጠሙ ያሉ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችንም በማጣራት ይፋ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም የታዋቂው አርቲስት ሀጫሉ ሑንዴሳ ግድያን ተከትሎ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥር ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸመው ዓይነተ-ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አንደኛው ነው፡፡

በወቅቱ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለማጣራት ኢሰመጉ በዋናው እና በቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በኩል መረጃዎችን በማሰባሰብ እና የመስክ ምርመራ ሥራዎችን በመሥራት ጥሰቶቹን በመለየት 147ኛውን ልዩ የሰብዓዊ መብቶች ዘገባ አጠናቋል፡፡

በመሆኑም፤ የምርመራ ሥራውን ግኝት የያዘውን የኢሰመጉ 147ኛው ልዩ የሰብዓዊ መብቶች ዘገባ በኢሰመጉ ዋና እና ቅርንጫፍ ቢሮዎች በኩል በአካል በመገኘት፤ እንዲሁም ከሚከተሉት የመገናኛ አማራጮች ያሻዎትን ተጠቅመው ማግኘት ይችላሉ፡፡