መቆሚያ ያጣው በመተከል ያሉ ሰዎች እልቂት!

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ – ኢሰመጉ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ መተከል ዞን፣ በቡለን፣ ድባጤ፣ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ እጅግ አሳስቦታል፡፡ ኢሰመጉ ታህሳስ
15 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ ንጹኃን ሰዎች መገደላቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ መሆናቸውን
አውግዞ፤ መንግሥት በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን የንጹኃን ሰዎች ሰቆቃ ለማስቆም የሚያስችል ፈጣን፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጅ ማሳሰቡ አይዘነጋም፡፡
ሆኖም፤ ከሰሞኑ ይኸው ችግር ዳግም ተከስቶ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ለኢሰመጉ ተናግራዋል፡፡ ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ የሚሄድ መኪና ውስጥ የነበሩ ተጓዦች ማንዱራ ከተማ ላይ በታጣቂዎች እንዲወርዱ ተደርጎ አንድ ሰው መገደሉን እና ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከጥር 2 – 3 ቀን 2013 ዓ.ም በቡለን እና ጉባ ወረዳዎች፣ ኦሜድላ እና አይነሸምስ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና መኖሪያ ቤቶችም መቃጠላቸውን ኢሰመጉ መረጃዎች ደርሰውታል፡፡
በሌላ በኩል፤ ‹‹በድባጤ ወረዳ፣ ቆርቃ ቀበሌ፣ ዳሌቲ በተባለች መንደር ትላንት ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ የኦነግ ሸኔ እና የቤኒን ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን፣ እስከአሁን ድረስ እኔ ራሴ ባለሁበት የ82 ሰዎች አስከሬን በፍለጋ መገኘቱን እና የቀብር ቦታዎች እየተዘጋጁ መሆኑን አይቻለሁ›› ሲሉ አንድ የዓይን እማኝ ለኢሰመጉ ተናግረዋል፡፡

ኢሰመጉ፤ በትላንትናው ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሊበለጥ እንደሚችል፣ በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን እና ከ24 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቆስለው በጋሊሳ ጤና ጣቢያ እና ቡለን ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

*

*